በቆላድባ አርሶአደሮች የግዳጅ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው

ሚያዝያ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከዚህ ቀደም በሰሜን ወሎ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች ሲካሄድ እንደነበረው አሁን ደግሞ በሰሜን ጎንደር አርሶአደሮች በግዴታ በእያካባቢያቸው ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው።
በቆላ ድባ ከተማ ከ150 በላይ አርሶአደሮች ተመልምለው ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ ሲሆን፣ የከተማው ነዋሪ ቅሬታውን ሲገልጽ ተገደው እንደገቡ ተናግረዋል። አንዳንድ ሰልጣኞች ስልጠናውን ካልተካፈሉ የጦር መሳሪያቸውን እንደሚቀሙ ማስፈራሪያ የደረሳቸው ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ከስልጠናው በሁዋላ ደሞዝ እንደሚቆረጥላቸው ተናግረዋል። ከሰልጠናው በሁዋላ የተለያዩ ወታደራዊ ግዳጆችን እንደሚፈጽሙ ተነግሯቸዋል።
በቆላ ድባ እና አካባቢዋ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ሃይል ተቀይሮ ባለፉት ወራት ተደጋጋሚ ጥቃቆት ሲፈጸሙ ቆይቷል። ስልጠናው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በአካባቢው ተወላጆች ለማጥቃት ሆን ተብሎ የታቀደ እቅድ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። አብዛኞቹ ሰልጣኞች እንደሚሉት ግን በእየለቱ የሚነገረውን የፖለቲካ ስብከት አብዛኛው ሰልጣኞች አይቀበሉትም።
በሌላ በኩል ደግሞ ሚያዚያ 24 ቀን 2009 ዓም በጎርጎራ ከተማ የሚገኘው የአመልድ ፕሮጀክት 6 ጽ/ቤቶች መቃጠላቸውን ተከትሎ አሁንም በአካባቢው ውጥረት እንደሰፈነ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ድርጊቱን የፈጸሙ ሃይሎችን ለመያዝ በሚል አሰሳው ተጠናክሮ መቀጠሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በባህርዳር ከተማ በህወሃት/ብአዴን ንብረትነት የሚታወቀውን የዳሸን ቢራ ምርት የሆነውን ባላገሩ ቢራን ለማስተዋወቅ የተጠራው የሙዚቃ ዝግጅት በቦንብ ፍንዳታ እንዲቋረጥ ከተደረገ በሁዋላ፣ የከተማውን ወጣቶች እየያዙ ማሰር መቀጠሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የኢህአዴግ ካድሬዎች የደረሰባቸውን ኪሳራ ለመሸፋፈን በሚል በጥርጣሬ ብቻ ወጣቶችን እየያዙ እያሰሩ መሆኑን ይገልጻሉ። አሁንም በርካታ ፖሊሶች በከተማው ተሰማርተው ጥበቃ እያደረጉ ነው።