ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2009)
መቀመጫውን በኦስትሪያ ቬይና ያደረገው አለም አቀፍ የፕሬስ ኢንስቲትዩት ከአለም አቀፉ የሚዲያ ድጋፍ (IMS) ጋር በጋራ እስክንድር ነጋ የአለማችን የ2017 የፕሬስ ነጻነት ጀግና በሚል ሰይመውታል።
አለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት ማክሰኞ ኤፕሬል 25, 2017 ከአውስሪያ መዲና ቬይና ባወጣው መግለጫ፣ ሃሳብን ለመግለፅ ነጻነት ወደር የሌለው ፅናትን ለሚያሳዩ የአለማችን ጋዜጠኞች የሚሰጠው ይኸው ሽልማት ለ2017 እስክንድር ነጋ መመረጡን አስታውቋል።
ላለፉት 6 አመታት ያህል በወህኒ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋር በአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የሚሰጠው ክብርና ሽልማት ወህኒ ቤት ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገው ፔን አሜሪካ የ2012 ተሸላሚ ያደረገው ሲሆን፣ ሽልማቱን ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካልም ፋሲል በተገኘችበት በኒውዮርክ ከተማ በሳይንስ ሙዝየም መካሄዱን ማስታወስ ተችሏል። በተመሳሳይ መቀመጫን ኒው ዮርክ ያደረገው ሂውማን ራይትስ ዎች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ጋር በጋራ የሸለመው ሲሆን፣ መቀመጫውን ጣሊያን ያደረገው የጋዜጠኞችና አሳታሚዎች ማህበር ወርቃማ የመጻፍ ነጻነት ብዕር የተባለውን ሽልማት ያበረከተለት ሲሆን፣ በጣሊያን ቱሪን የሽልማት ስነ-ስርዓቱም ተካሄዷል። አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል የህሊና እስረኛ ሲል ሰይሞታል።
አለም አቀፍ የፕሬስ ኢንስቲትዩት IPI የ2017 የፕሬስ ነጻነት ጀግና በሚል በዚሁ አመት የመረጠው ጋዜጠኛ እስክንድር የሽልማት ስነ-ስርዓቱ የፊታችን ግንቦት 10 ፥ 2009 በጀርመን ሃምቡርግ ከተማ ይካሄዳል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋር መስከረም 3 ፥ 2004 ወህኒ የወረደ ሲሆን፣ የ18 አመታት አስራትም ተፈርዶበታል። ላለፉት 6 አመታት በወህኒ የቆየው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋር በአለም አቀፍ ተቋማት ብቻ ሳይሆን፣ በመንግስታት በተለይም በዩ ኤስ አሜሪካ ጭምር ለፕሬስ ነጻነት የታሰረ በሚል ተወድሷል። የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በስልጣን ዘመናቸው የፅናት ተምሳሌት ሲሉት በአደባባይ እንዳወደሱት ይታወሳል።