የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለግል ባለሃብቶች የሚሰጠውን የኢንቨስትመንት ብድር አቋረጠ

ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያወጣውን አዲስ መመሪያ ተከትሎ ንግድ ባንክ ለረጅም አመታት ለግል ባለሃብቶች ሲሰጥ የቆየውን ብድር ከሚያዚያ 2 ፥ 2009 አም ጀምሮ ማቋረጡን ካፒታል የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።

ብሄራዊ ባንክ ከንግድ ባንክ ብድር እንዳያገኙ የተደረጉ ባለሃብቶች ጥያቄያቸውን ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በማቅረብ እንዲያስተናግዱ ትዕዛዝ መስጠቱ ታውቋል።

በዚሁ የብሄራዊ ባንክ አዲስ መመሪያ መሰረት የብድር ጥያቄን አቅርበው ውሳኔን በመጠባበቅ ላይ የነበሩም ሆነ አዲስ ብድር ጠያቂ ባለሃብቶች የብድር ጥያቄያቸውን ወደ ልማት ባንክ እንዲያዛውሩ ተጠይቀዋል።

ይሁንና መንግስት የወሰደው ዕርምጃ የብድር ጥያቄን አቅርበው ባሉ በርካታ ባለሃብቶች ዘንድ መጉላላትን ሊፈጥር እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።

የብሄራዊ ባንክ አዲሱ መመሪያ የሃገሪቱን ልማት ለማጠናከር የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን ገልጾ፣ በቀጣዩ ሳምንት በብድሩ ዙሪያ ማብራሪያን እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ሰፋፊ መሬትን ለእርሻ ስራ በሊዝ የሚወስዱ ባለሃብቶች የተለያዩ ማሽነሪዎችን የሚገዙና ህንጻዎችን የሚገነቡ ባለሃብቶች ከንግድ ባንክ ሲያገኙ የቆዩ ብድር እንዲቀር ተደርጓል።

ይሁንና እነዚህ ባለሃብቶች ላቋቋሟቸው ፕሮጄክቶች ስራ ማከናወኛ ከባንኩ ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ ይመቻቻል ተብሏል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው መንግስት የወሰደው ዕርምጃ ሃገሪቱ ያጋጠማትን የፋይናንስ እጥረት ተከትሎ እንደሆነ ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቀጣይ ለሚሰጣቸው ብድሮች ባለሃብቶች 70 በመቶ ወጪ እንዲያሳዩ በቅርቡ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።

የልማት ባንክ የብድር ወለድ መጠኑንም ከ9.5 በመቶ ወደ 12.5 በመቶ ያሳደገ ሲሆን፣ ወደ ባንኩ ብድርን ለማግኘት የሚሄዱ ባለሃብቶች ተጨማሪ የፕሮጄክት ወጪ ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

የፕሮጄክት ወጪዎች መጨመር በቀጣይ ኩባንያዎች በሚያመርቷቸው ምርት ላይ የዋጋ ጭማሪን በማስከተል ድርጊቱ የሃገሪቱ የዋጋ ግሽበት እንዲጨምር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ወደ ልማት ፕሮጄክት የሚገቡ ባለሃብቶች እንዲያስይዙና እንዲያሳዩ ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታም በባለሃብቶች ላይ ጫናን እንደሚያሳድር የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የብሄራዊ ባንክ በቅርቡ በአስመጭነት ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለመክፈት ሙሉ ክፍያን እንዲፈፅሙ አዲስ መመሪያን ማውጣቱ ይታወሳል።

የመመሪያውን መውጣት ተከትሎ ባለሃብቶች በግል ባንኮች ያላቸውን ተቀማጭ ገንዘብ በማውጣት ወደ ንግድ ባንክ ማስገባታቸውንና ድርጊቱ በግል ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ የባንክ ባለሙያዎች ሲገልፁ ቆይተዋል።

የብሄራዊ ባንክ በየጊዜው እያወጣ ያለው አዳዲስ መመሪያ የግል ባንኮችን ህልውና እየተፈታተነ እንደሚገኝ የባንክ ባለሙያዎች በመግለጽ ላይ ሲሆኑ፣ ይኸው ሁኔታ ባንኮች ያለፍላጎታቸው እንዲጣመሩ የሚያደርግ መሆኑንም ተነግሯል።