ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ለሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን የኮሌራ በሽታ ስርጭት (ወረርሽኝ) በቁጥር ስር ለማዋል የውጭ ሃገራት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የፈረንሳዩ አለም አቀፍ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ግብረ ሰናይ ድርጅት ጥሪውን አቀረበ።
በክልሉ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ላይ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ፣ ከ16 ሺ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ይፋ አድርጓል።
የፌዴራልና የክልሉ ባለስልጣት በበሽታው ስርጭት ሳቢያ በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ቢያረጋግጡም የሟቾችን ቁጥር ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
በተለያዩ ዞኖች የኮሌራ በሽታውን ስርጭት ለመግታት ወደ 1ሺ 200 አካባቢ የሃኪሞች ቡድን እንዲሰማራ የተደረገ ሲሆን፣ አዳዲስ የክልሉ ቀበሌዎች በበሽታው ስርጭት ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን የፈረንሳዩ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ተቋም አስታውቋል።
የክልሉ የጤና ቢሮ ሃላፊዎች በየወሩ 3ሺ 500 አካባቢ ሰዎች በበሽታው እየተያዙ ወደ ህክምና ተቋማት እንደሚመጡ ገልጸዋል።
በኮሌራ ወረርሽኙ የሚያዙ ነዋሪዎችን ለመታደግ 100 ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ተቋማት የተቋቋሙ ሲሆን፣ በዶሎ ዞን ስር የሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ተመልክቷል።
በሶማሌ ክልል በመዛመት ላይ ያለውን ይህንኑ የበሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር የውጭ ሃገራት ድጋፍ በአፋጣኝ እንደሚያስፈልግ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ጥሪውን አቅርቧል።
ንፁህ የውሃ አቅርቦትን በበሽታው ለተያዙ ሰዎች የማድረሱ ጥረት በመሰረተ ልማት አለመሟላትና በቁሳቁሶች እጥረት እክል እየገጠመው እንደሚገኝ የፈረንሳዩ ድንበር የለሽ የሃኪሞች (ሜዲሲን ሳን ፍሮንቲየርስ) በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።
በክልሉ ወደ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ የሚጠጉ ሰዎችን ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ አጋልጦ የሚገኘው የድርቅ አደጋ ዕልባት አለማግኘቱ የኮሌራ በሽታው እየተባባሰ እንደሄደ አስተዋፅዖ ማድረጉን የእርዳታ ድርጅቶች ይገልጻሉ።
በክልሉ ድርቁንና የኮሌራ በሽታ ስርጭቱ ለመቆጣጠር የሚያስፈልገው ድጋፍ በአፋጣኝ የሚገኝ ካልሆነ የበርካታ ተጨማሪ ሰዎች ህይወት አደጋ ውስጥ እንደሚሆን በኢትዮጵያ የግብር ሰናይ ድርጅቱ ሃላፊ ኦሊቨር ሲልዝ (Oliver Schulz) አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ያለው የኮሌራ በሽታ መባባስን ተከትሎ በሃገሪቱ ያሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በጀታቸውን በሽታውን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ርብርብ እንዲያዞሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መጠየቁ ይታወሳል።
የአለም አቀፉ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በበኩሉ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር በአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ ከፍ ማለቱን ሰኞ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ይሁንና የፌዴራል መንግስት ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ቢያረጋግጥም ቁጥሩን ግን ከመግለፅ ተቆጥቦ ይገኛል። የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድርቁን ለመታደግ ይሰጣል ተብለው የሚጠበቀው ድጋፍ በወቅቱ አለመገኘቱ ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉም ተነግሯል። ይሁንና መንግስት ድርቁን ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ ነው ሲል በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል።