ሚያዝያ ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ አሰፋ ጫቦ ከአባታቸው አቶ ሰዴ ሃማ ከእናታቸው ወ/ሮ ማቱኬ አጆ በቀድሞው አጠራር በጋሞጎፋ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ በጨንቻ ከተማ 1936 ዓ.ም ተወለዱ።
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በቤተክህነት ውስጥ ፊደል በመቁጠር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን እስከ ድቁና ማእረግ በመድረስ አገልግለዋል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጨንቻ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ደግሞ ሻሸመኔ እና አዲስ አበባ ኮከበጽባህ ትምህርት ቤት ተከታለዋል። የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በLLB አጠናቀዋል።
አቶ አሰፋ ጫቦ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት በኢትዮጵያ አቪየሽ፣ የአጥቢያ ፍ/ቤት ጸሐፊ፣ የበጅሮንድ ጽ/ቤት ሰራተኛና ጸሐፊነት፣ የአየር ትንበያ (metrology) የሕግ አማካሪ በመሆንም አገራቸውን አገልግለዋል። በደርግ ስርዓትም ኢጭአትን ከመሰረቱት ዋነኛዎች አንዱ ሲሆኑ በጋሙጎፋ ክፍለሃገር የጋርዱላ አውራጃ አስተዳዳሪ በመሆንም ሰርተዋል። በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያትም በማእከላዊ እስር ቤት ታስረው አስር ዓመት ከስድስት ወራት በወሕኒ ቤት አሳልፈዋል። የህወሃት ኢህዴግ ገዥዎች መንበረ ስልጣኑን በተቆጣጠሩበት በሽግግር ወቅት የኦሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦሞቲክ) መስራች እና የፓርቲው ሊቀመንበር በመሆን የሽግግር መንግስቱ ላይ ተሳትፈዋል። የህወሃት ኢህአዴግን መንግስትን በመቃወማቸው ለስደት ተዳርገው ሕይወታቸው እስካለፈበት እለት ድረስ በአሜሪካ ኖረዋል።
የሕግ ባለሙያ፣ ደራሲ ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ፖለቲከኛ አቶ አሰፋ ጫቦ ባድረባቸው ድንገተኛ ህመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ73 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። አቶ አሰፋ ጫቦ የአራት ልጆች አባትና የዘጠኝ ልጆች አያት ነበሩ። ኢሳት ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።