ሶስት የፖለቲካ ድርጅቶች ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲባባስ አድርገዋል ተብለው ክስ ሊመሰረትባቸው መሆኑን ታወቀ

ኢሳት (ሚያዚያ 13 ፥ 2009)

ሶስት የፖለቲካ ድርጅቶች ከአንድ አመት በፊት በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲባባስ አድርገዋል ተብለው ክስ ሊመሰረትባቸው መሆኑን ታወቀ።

ከቀናት በፊት በህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲመረምር የቆየው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ሶስት የፖለቲካ ድርጅቶች ተቃውሞ እንዲቀሰቅስና እንዲባባስ የተለያዩ አስተዋጽዖ አድርገዋል ሲል ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል። የኮሚሽኑን ሪፖርት ያቀረበው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ ህዝባዊ ተቃውሞን አባብሰዋል በተባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ክስ እንዲመሰረት ሃሙስ ውሳኔን ሰጥቷል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሰማያዊ ፓርቲ እና የጌዲዮ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ክስ እንዲመሰረትባቸው የተወሰነ መሆኑን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

ኦፌኮ እና ሰማያዊ ፓርቲ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ህዝባዊ ተቃውሞዎች እንዲባባስ አስተዋጽዖ አድርገዋል ተብለው ህጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው የተወሰነ ሲሆን የጌድዮ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች በበኩሉ በጌዲዮ ዞን የዘር ግጭት እንዲቀንስ አድርጓል ተብሏል።

በሶስቱ ክልሎች ከተካሄዱ ተቃውሞዎች ጋር በተገናኘ 669 ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለፓርላማ አቅርቦ በነበረው ሪፖርት አመልክቷል።

ይኸው ሪፖርት ሃሙስ ለፓርላማ አባላት ለውይይት ቀርቦ እንዲጸድቅ የተደረገ ሲሆን፣ የፓርላማ አባላቱ በአብዛኛው ድምፅ ሶስቱ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲከሰሱ ድምፅ ሰጥተዋል። የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ዕርምጃው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ህልውና በፍ/ቤት በመሰረዝ ህጋዊነታቸውን ያሳጣቸዋል።

መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የፖለቲካ ድርጅቶቹን ተጠያቂ ከማድረጉ በተጨማሪ የሃይል ዕርምጃን ወስደዋል የተባሉ የጸጥታ አባላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መወሰኑ ይታወሳል።

ይሁንና ምክር ቤቱ ተጠያቂ እንዲሆኑ በተወሰነው የጸጥታ አባላት ላይ የሰጠው ትዕዛዝ የለም።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት የሶስት ወር ዕርምጃ 699 ሰዎች መሞታቸውን ቢገልፅም አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር ግን በሪፖርቱ አለመካተቱንና ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ከተገለጸው ቁጥር በላይ መሆኑን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋምት ይገልጻሉ።

ኮሚሽኑ ጥናቱ ከሃምሌ 2008 አም እስከ መስከረም 2009 አም መሸፈኑን አመልክቷል። ይሁንና ከሃምሌ ወር በፊት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች  ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ እንደነበርና ከ100 የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን መንግስት በወቅቱ ማረጋገጡ አይዘነጋም።

ህዝባዊ ተቃውሞን ለመቆጣጠር መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፣ የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ በርካታ ሰዎች መገደላቸውንን ከ24 ሺ በላይ ሰዎችም ለእስር መገደላቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ሲገልጽ ቆይቷል።

አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራቶች እንዲራዘም መደረጉን እስራትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲባባስ ማድረጉን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይገልጻሉ።