በወሎ ለእርዳታ የመጣ እህል መዘረፉን ነዋሪዎች ተናገሩ በሙስና እና በአስተዳደር ችግር የተማረሩት ዜጎች መንግስት አለ ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ።

መጋቢት ፳፰ (ሃያ ስምንት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ሳምንት በወሎ በተደረገው ስብሰባ ለእርዳታ የተላከ እህል፣ ዘይት፣ ክክ እና ሌሎችም ነገሮች እየተዘረፉ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አለባቸው አረጋ፣ ሰራተኞች በሞቱ ሰዎች ሳይቀር እየፈረሙ ገንዘብ ይወስዳሉ ይላሉ። ነዋሪዎቹ 100 ኩንታል የእርዳታ ስንዴ በባለስልጣናት መዘረፉንም ይገልጻሉ ። ልማት የለም የሚሉት አቶ አለባቸው፣ ስኳር እና ዘይት ካየን 5 ወራት አልፎናል ብለዋል።
መሬት በአምቻ ጋብቻ ነው የሚሰጠው የሚሉት አቶ ጸጋየ አድማሱ ደግሞ፣ ቦታ የሚሰጠው ለካቢኔ አባላት ነው ይላሉ። “ ህዝቡአንድ ቁና ስንዴ ለማግኘት እስከ 8 ሰአት ይጓዛል፤ ከዚያም 3 ቀን ድረስ ጠብቅ ይባላል። በእነዚህ ሶስት ቀናት ውስጥ 200 ብር ድረስ አጥፍቶ ይሄዳል፤ አንድ ቁና ስንዴ ግን 80 ብር ነው፤ እንዲህ በማድረግ ፣ ህዝቡ በረሃብ እያለቀ የእርዳታውን ስንዴ እነሱ እየዘረፉት ነው” በማለት አጋልጠዋል።
አቶ ጸጋየ እርሳቸው እና በስራቸው ያሉ ሰራተኞች ለባለስልጣናት ጉቦ መስጠታቸውን ያጋልጣሉ።
አቶ አስናቀው ታደለ ደግሞ ይህ መንግስት አለ ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ።