በመላው አገሪቱ በሚገኙ ወረዳዎች መብራት የለም በሚባልበት ደረጃ ላይ መደረሱን መረጃዎች አመለከቱ

መጋቢት ፳፰ (ሃያ ስምንት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከህዝብ ያሰባሰቡትን መረጃ አጠናክረው የላኩትን መረጃ በማድረግ በጻፈው ደብዳቤ በመላ አገሪቱ የሚታየው የመብራት መቆራረጥ ህዝቡን ተስፋ አስቆርጦታል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽ/ቤት ፣ በፓርላማ አባላት አማካኝነት ከህዝብ ያሰባሰባቸውን 66 ገጽ ጥያቄዎችን ለውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የላከ ሲሆን፣ ጥያቄዎቹ በአብዛኛው በመብራት መቆራረጥ፣ በትራንስፎርሜሽን እጥረት ፣ በምሰሶ እና ሳህን መውደቅ፣ በቆጣሪ ችግር የተሞሉ ናቸው።
በትግራይ ክልል በኩናማ ወረዳ ለ11 አመታት መብራት ተጠይቆ መፍትሄ አጥተዋል። በአድዋ ለውሃና ለመብራት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ቢሰበሰብም ገንዘቡ ባክኖ ቀርቷል። በአስገደ ጽምብላም እንዲሁ 2 ሚሊዮን ብር ለመብራት ተብሎ ቢሰበሰብም ስራው ሳይጀመር ገንዘቡ የት እንደገባ አይታወቅም።
በበየዳ እና በጠለምት 25 አመታት ሙሉ የወረዳው ህዝብ መብራት አላገኘም። በወልቃይት ጠገዴ ደግሞ ከ55 ቀበሌዎች መብራት ያገኙት 6 ብቻ ናቸው። በመተማ 5 ሚሊዮን 500 ሺ ብር ህዝቡ ቢያዋጣም መልስ አልተገኘም።
በደቡብ ጎንደር በረብ መስኖ ግድብ ባካናል ስራ መሬታቸው የተወሰደባቸው አርሶአደሮች የታሰበላቸው የካሳ ግምት ተገቢ ኤኢደለም በሚል ቅሬታ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው እንዳላገኙ እንዲሁም የተገመተላቸውንም ቢሆን በወቅቱ አለማገኘታቸው በሪፖርቱ ተመልከቷል።
የርብ መስኖ ፕሮጀክትም በተያዘለት ጊዜ አልተጠናቀቀም፤ ፕሮጀክቱ 14 ሺ ሄክታር መሬት ያለማል ተብሎ ከተነገረ በሁዋላ ማልማት የሚችለው 3 ሺ ሄክታር ብቻ ነው መባሉ ቅሬታ መፍጠሩም ተጠቅሷል።
በአውሮፓ ህብረት እርዳታ የሚሰራው የሞጣ ውሃ ፕሮጀክት በ2003 ዓም ተጅምሮ በ2005 ይጠናቀቃል ቢባልም፣ እስካሁን ባለመጠናቀቁ ህዝቡ አቤቱታ ማቅረቡ እንዲሁም የጨሞጋ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተግባራዊ አለመሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
በአፋር ከሩቅ አካባቢዎች እህል ለማስፈጨት የሚመጡ ሰዎች በመብራት መጥፋት ምክንያት እንደሚያድሩና በህይወታቸው ላይ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑ፣ በአደር ወረዳ ደግሞ 8 መንደሮች ለጥቂት ቀናት መብራት ካገኙ በሁዋላ ላለፉት 3 አመታት መብራት አግኝተው እንደማያውቁ ተጠቅሷል።
በጋምቤላም የመብራት ችግር ከፍተኛ መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል። በአገሪቱ የተለያዩ ወረዳዎች ያለውን የመብራት እና የውሃ ችግር 66 ገጽ ሪፖርት በኢሳት የፌስ ቡክ አካውንት እና በድረገጻችን ላይ ስለምናስቀምጠው ሙሉውን ለማንበብ እንደምትችሉ ለመግልጽ እንወዳለን።