ኢሳት ( መጋቢት 27 ፥ 2009)
የሱዳኑ ፕሬዚደንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካና በወታደራዊ ዘርፎች ትስስር ለመመስረት የሚያስችል አዲስ ስምምነት መደረሱን አስታወቁ።
ለሶስት ቀን ጉብኝት ማክሰኞ አዲስ አበባ የገቡት ፕሬዚደንት አል-በሽር የኢትዮጵያ ደህንነት እና ፀጥታ ከሱዳን ተለይቶ አይታይም ሲሉ ለጋዜጠኞች መግለጻቸውን ሱዳን ትሪቢዮን ጋዜጣ ዘግቧል።
ካለፈው አመት ጀምሮ ለሶስተኛ ጊዜ የሁለትዮሽ ስምምነት የደረሱት ሁለቱ ሃገሮች የፖሊስ የደህንነትና የሰራዊት ተቋማቸው ተቀናጅተው እንዲሰሩ ስምምነት መደረሱንም ይፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ የሱዳን ወታደራዊ አካላት በቅንጅት ለመስራት የደረሱት አዲሱ ስምምነት በሁለቱ ሃገራት መካከል ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን ቅድሚያ እንደሚሰጥ አልበሽር ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው የሱዳን ማንኛውም ስጋት የኢትዮጵያ የብሄራዊ የደህንነት ስጋት ነው ሲሉ ስምምነቱን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ሁለቱ ሃገራት በወታደራዊ ኢኮኖሚያዊና ተጓዳኝ ጉዳዮች ዙሪያ ተባብረው ለመስራት ከደረሱት በተጨማሪ በቅርቡ ነጻ የንግድ ቀጠናን ለማቋቋም መስማማታቸው ታውቋል።
የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር በቅርቡ ከግብፅ ጋር በሜዲትራኒያን ባህር ዙሪያ በሚገኝ አዋሳኝ ይዞታ ላይ በይገባኛል ውዝግብ ውስጥ ከገቡ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር ዘርፈ ብዙ ስምምነት ሲደርሱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የቱርኩ ዜና አገልግሎት አናዱሉ ዘግቧል።
ከግብፅ ጋር አዲስ ቅራኔ ውስጥ የሚገኙት ፕሬዚደንት አልበሽር የአባይ ወንዝን በፍትሃዊነት ለመጠቀም ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት መደረሱንም ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
ሃገራቸው በመገንባት ላይ ካለው የአባይ ግድም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት ፍላጎት እንዳላትና የአባይ ተፋሰስ ሃገራት ከወንዙ የመጠቀም መብት እንዳላቸው አልበሽር አክለው ገልጸዋል።
የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ከአንድ አመት በፊት ተመሳሳይ ስምምነቶችን በደረሱ ጊዜ የጋራ ድንበራቸውን ለማካለል ስምምነት መደረጉን ቢገልፁም በአዲሱ የመግባቢያ ሰነድ የድንበር ጉዳይ በመሪዎች ሳይነሳ ቀርቷል። የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሱዳን በአባይ ወንዝ አጠቃቀም እና በግድቡ ላይ ደርሰናል ያሉት አዲስ ስምምነት የአባይ ወንዝ አይነካ የሚል አቋም ላላት ግብፅ መልዕክትን ለማስተለልፍ ያለመ እንደሆነ ለቱርኩ ዜና አገልግሎት አስረድተዋል።
የአዲስ አበባውን አዲስ ስምምነት የእከክልኝ ልከክህ አይነት ነው ሲሉ የገለጹት የፖለቲካ ተንታኞች ሁለቱ ሃገራት እርስ በርስ በመደጋገፍ የብሄራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር እየሞከሩ እንድሆነ አክለው ገልጸዋል።