የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቂሊንጦ የደርሰውን የእሳት ቃጠሎ ያስነሱት እስረኞች ናቸው ሲል ለፓርላማ ገለጸ

ኢሳት ( መጋቢት 27 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው አመት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ደርሶ የነበረው የእሳት ቃጠሎ አደጋ ያስነሱት በወንጀል ተጠርጥረው የፍርድ ሂደትን የሚጠባበቁ እስረኞች ናቸው ሲል ለፓርላማ ገለጸ።

በአጀንዳው ዙሪያ ያካሄደው ጥናት አስመልክቶ ለፓርላማው ሪፖርቱን ረቡዕ ያቀረበው መንግስታዊው ኮሚሽን ከዚሁ በፊት ከሳሽ አቃቤ ህግ እስረኞቹን ተጠያቂ ያደረገበት ሂደት በተመሳሳይ ሁኔታ አቅርቧል።

ባለፈው አመት ነሃሴ ወር በእስር ቤቱ ላይ ደርሶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ 21 እስረኞች በጭስ ታፍነው መሞታቸውንና ሁለቱ ደግሞ ሊያመልጡ ሲሉ በበተኮሰባቸው ጥይት መሞታቸውን በሪፖርቱ አመልክቷል።

38 በሚሆኑ የእስር ቤቱ ተከሳሾች ላይ ተደራራቢ ክስ መስርቶ የሚገኘው ከሳሽ አቃቤ ህግ እስረኞቹ የእሳት ቃጠሎው እንዲደርስ ምክንያት  ሆነዋል በማለት ለሞቱት ሰዎች ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል።

ተከሳሾቹ በበኩላቸው አቃቤ ህግ ያቀረበባቸው የወንጀል ክስ እንዳልፈጸሙ ለፍርድ ቤት ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት ተከሳሾች የእስር ቤቱ የጸጥታ አባላት ቃላቸውን ያለ ፍላጎታቸው እና በሃይል እንዲሰጡ በማድረጋቸው ፍርድ ቤቱ የሰጡትን የእምነት ቃል ውድቅ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙ እነዚሁ ተከሳሾች በተደጋጋሚ በእስር ቤቱ ይፈጸምብናል ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምርመራ እንዲካሄድበት ጉዳያቸውን እየተከታተለ ያለው ፍርድ ቤት መወሰኑም ይታወሳል።

በእስር ቤቱ ድርሶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ ተመሳሳይ ምርመራን ሲያሄድ የነበረው ኮሚሽኑ በእስር ቤቱ መግባት የሌለባቸው አደንዛዥ እጾችን ጨምሮ ላይተር እና ለቃጠሎ የሚዳረጉ ቁሳቁሶች መታየታቸውን ባቀረበው ሪፖርት ማመልከቱን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሪፖርቱ ዋቢ በማድረግ በዘገባቸው አቅርበዋል።

ይሁንና ኮሚሽኑ ወደ እስር ቤት ገብተዋል ያላቸውን እነዚሁ ቁሳቁሶች በማን እና እንዴት ሊገቡ እንደቻለ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ በእስር ቤቱ የሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ ድርጊቶችን እና የእስረኞችን አያያዝ መኖራቸውን ግን አረጋግጧል።

ኮሚሽኑ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ የሰጠው መረጃ የሌለ ሲሆን፣ ለተወካዮቹ ምክር ቤት ፍትህ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርቱ በቅርቡ ለፓርላማ በማቅረብ ሪፖርቱ ውይይት እንዲደረግበት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

አደጋው በደረሰ ጊዜ በእስር ቤቱ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች እንዲሁም አንድ ያልታጠቀ የጸጥታ አባል የቂሊንጦ እስር ቤት ጠባቂዎች በእስረኞች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ለመገናኛ ብዙሃን መግለጻቸው ይታወሳል።