ኢሳት (መጋቢት 19 ፥ 2009)
የአለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አራት ክልሎች በመባባስ ላይ ባለው አዲስ የድርቅ አደጋ በ192 ወረዳዎች በአንደኛ ደረጃ በመመደብ አፋጣኝ የምግብ አቅርቦት እንደሚፈልጉ አስታወቀ።
በእነዚሁ ክልሎች የድርቁ አደጋ መልኩን እየቀየረ በመሄድ ላይ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ በአራቱ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ዕድሚያቸው ከአምስት አመት በታች የሆነ 198 ሺ ህጻናትና 120ሺ በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች ልዩ የምግብ እንክብካቤን የሚሹ እንደሆነም ይፋ አድርጓል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማት በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ያለው የድርቅ አደጋ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ይሆናል ሲሉ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
ወርልድ ቪዥን የተሰኘ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅት በኢትዮጵያ እንዲሁም በሶማሊያ ደቡብ ሱዳንና ኬንያ ወደ 700ሺ የሚጠጉ ህጻናት ከድርቅ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል ሰኞ ማሳሰቡ ይታወሳል። በዚሁ የድርቅ ዙሪያ ማክሰኞ መግለጫን ያወጣው የአለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሶማሌ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ያለው የምግብ እጥረት እየተባባሰ መምጣቱን ገልጿል።
በተያዘው ወር በ192 ወረዳዎች ልዩ ክትትልን የሚሹ ተብለው በአንደኛ ደረጃ መቀመጣቸውንና በሶማሌ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አክሎ አስታውቋል።
ድርቁ በመባባስ ላይ ቢሆንም ለተረጂዎች የሚፈለገው ዕርዳታ አለመገኘቱ ለእርዳታ ድርጅቶች አስቸጋሪ ሆኖ እንደሚገኝም የአለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።
ይኸው የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋም በሶማሌ ክልል ብቻ ዕርዳታ ሊደረግላቸው ያቀዳቸው የተረጂዎች ቁጥር ከ1.2 ሚሊዮን ወደ 1.6 ሚሊዮን ማሻቀቡን አክሎ አመልክቷል።
በሃገሪቱ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ ከተጋለጡ 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መካከል ወደ 2 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑት በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል የሚገኙ ሲሆን፣ የድርቁ አደጋ ወደ ረሃብ ሊለወጥ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ ለተረጂዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እቅድን ይዞ የነበረ ቢሆንም በአካባቢው በገበያ የሚገኝ የምግብ አቅርቦት ባለመኖሩና በዋጋ መናር ምክንያት የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ መደረጉንም ለመረዳት ተችሏል።
አማራጭ ድጋፍን ለተረጂዎች ማቅረብ ያልቻለው ድርጅቱ ወደ ሁለት ሚሊዮን ለሚጠጉት ሰዎች የምግብ ድጋፍን በአፋጣኝ ማቅረቡ ብቸኛው መፍትሄ ሆኖ መገኘቱንም አመልክቷል።
በሶማሌ ክልል ለተረጂዎች የገንዘብ ክፍያ ለማድረግ የተያዘው እቅድ ባይሳካም በተያዘው ወር በአማራና ኦሮሚያ ክልል ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ሰዎች ገንዘብ የመስጠቱ ድጋፍ ቀጣይ እንደሚሆን አክሎ ገልጿል።
ይሁንና በሶማሌ ክልል ተረጂዎች በሚሰጣቸው የገንዘብ ድጋፍ የሚገዛ ምግብ ባለመኖሩና የምግብ ዋጋ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ ፕሮግራሙ እንዲቀር መደረጉ ታውቋል።
የክልሉ ባለስልጣናት በበኩላቸው በድርቁ ሳቢያ በአንድ ዞን ብቻ እስካሁን ድረስ ወደ 40 ሺ አካባቢ የቁም እንስሳት መሞታቸውንና ከ25 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ይፋ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ስር በሚገኙ በጀረር፣ ቆራሄ፣ እና ዶሎ ዞኖች ያለው የድርቅ አደጋ በእንስሳትና በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ይነገራል።