የውጭ ንግድ ባለፉት ስድስት ወራት ከታቀደው ገቢ 1 ቢሊዮን ብር ጉድለት አስመዘገበ

ኢሳት (መጋቢት 19 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ ውጭ ንግድ ባለፉት ስድስት ወራቶች ብቻ ሊያስገኝ ከታቀደው ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት አስመዘገበ።

ሃገሪቱ በተያዘው በጀት አመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከውጭ ንግድ ዘርፍ 4.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት እቅድ የነበራት ቢሆንም፣ ሊገኝ የቻለው ግን 1.4 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል። ባለፉት ስድስት ወራቶች የውጭ ንግድ ገቢው ከታቀደው በታች  ማስመዝገቡ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴውና በውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ጫናን እንደሚያሳድር የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ውጭ ንግድ ካለፉት ሶስትና አራት አመታት ወዲህ በማሽልቆል ላይ ሲሆን፣ በ2008 አም 2.8 ቢሊዮን ዶላር ከ2007 አም ከተገኘው ጋር ሲነጻጸር በ139 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ ማሳየቱም ታውቋል።

በተለይ የሃገሪቱ የቡናና የሌሎች የግብርና ምርቶች ውጤቶች የውጭ ንግድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማሽቆልቆልን በማስመዝገብ ላይ ሲሆን የህገ-ወጥ ንግድ መበራከት እንዲሁም የጥራት መጉደልና ከባንኮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ለውጭ ንግድ ገቢው ማሽቆልቆል ከተቀመጡ ምክንያቶች ዋነኞቹ ናቸው።

በኢትዮጵያ ባለፈው አመት ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲሁም የድርቅ አደጋ በግብርና ምርት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ላይ ጫናን ያሳደሩ ሲሆን፣ የግብዓትና የጥራት እንዲሁም በመንግስት በኩል ያለ የአሰራር ቅልጥፍና ማነስ ደግሞ በኢንዱስትሪ ምርቶች ውጭ ንግድ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን የንግድ ሚኒስቴር ይገልጻል።

ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት የውጭ ንግድ ዘርፉን ለመታደግ አማካሪ ምክር ቤት እንዲቋቋም መወሰኑ ይታወሳል። አዲስ የተቋቋመው ምክር ቤት በውጭ ንግድና በውጭ ምንዛሪ ክምችት እየታዩ ያሉ ችግሮችን ዕልባት ለመስጠት ሃላፊነት እንደተጣለበት ታውቋል።

ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ የንግድ ሸቀጣሸቀጦች ገቢ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ወደ ሃገሪቱ ተመልሶ አለመግባትም ለኢኮኖሚውና ለውጭ ምንዛሪ ክምችት መቀነሱ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ሲገልፁ ቆይተዋል። በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ከውጭ ሃገር የሚገቡ ቁሳቁሶች ዋጋ በየዕለቱ በመጨመር ላይ መሆኑንም ተጠቃሚዎች ይገልጻሉ።