ኢሳት (መጋቢት 19 ፥ 2009)
የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በመሆን የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ውለዋል ተብለው ለእስር ከተዳረጉ 21 ሰዎች መካከል 16ቱ ከአራት እስከ 13 አመት በሚደርስ ፅኑ ዕስራት እንዲቀጡ ማክሰኞ ወሰነ።
ተከሳሾቹ በአዲስ አበባና በሶስት የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ነዋሪዎች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሁሉም ግለሰቦች የሃገሪቱን ህዝቦች አንድነት የማፈራረስና የኦሮሚያ ክልልን ከፌዴሬሽኑ የመገንጠል አላማ ይዘው ተንቀሳቅሰዋል ሲል የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በክሱ አቅርቧል።
አቃቤ ህግ የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው 16ቱ ግለሰቦች አባላትን በመመልመል ምዕራብ ሸዋ ዞን አድአ በርጋ ወረዳ ኦሎን ኮሚ አካባቢ በሚገኘው በሩዴ ጫካ ውስጥ ለሚገኘው የሽብር ድርጅት ታጣቂዎች የስንቅና የትጥቅ ድጋፍ ማድረጋቸውንም በክሱ ዘርዝሮ እንደነበር የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ይሁንና ከሳሽ አቃቤ ህግ በሩዴ ጫካ ውስጥ ይገኛሉ ስላላቸው ታጣቂዎች ሁኔታ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ በመንግስት በኩል የተወሰደ ዕርምጃ ይኑር አይኑር የታወቀ ነገር የለም።
ተከሳሾቹ ከመጋቢት ወር 2007 አም ጀምሮ የሽብር ጥቃትን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን በክሱ ቢዘረዘርም ግለሰቦቹ የፈጸሙት ድርጊት አለመኖሩ ተመልክቷል።
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 16ቱ ተከሳሾች ከአራት እስከ 13 አመት በሚደረስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሰዎች የኦነግ አባላት ናችሁ እየተባሉ ለእስር ሲዳረጉ መቆየታቸውን ሂማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።
እነዚሁ አካላት የኦነግ እንዲሁም የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር አባልና ደጋፊዎች ናችሁ የተባሉ ግለሰቦች የሽብርተኛ ወንጀል ክስ እየተመሰረተባቸው ለረጅም እስር ሲዳረጉ መቆየታቸውን ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅትም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የዚሁ ድርጊት ሰለባ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። አለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ሃገራት የኢትዮጵያ መንግስት ከአመታት በፊት ተግባራዊ ያደረገው የሽብርተኛ ወንጀል ህግ በመንግስት ላይ ትችትን የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችንና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን እንዲሁም አባላትን ለማፈን የወጣ ነው ሲሉ ህጉ ማሻሻያ እንዲደረግበት ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ሃሳባቸውን በነጻነት ለመግለጽ የሞከሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በዚሁ አዋጅ መሰረት ለእስር ተዳርገው ይገኛሉ።