የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ለእስር ከተዳረጉት ውስጥ 5 ሺ የሚሆኑት ክስ ሊመሰርትባቸው መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 19 ፥ 2009)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ ለእስር ከተዳረጉ ከ20ሺ በላይ ሰዎች መካከል አምስት ሺ የሚሆኑት ክስ ሊመሰርትባቸው መሆኑ ተገለጸ።

በጥቅምት ወር በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመጽ ለመቆጣጠር ተግባራዊ የተደረገውን ይህንኑ አዋጅ ምክንያት በማድረግ 26ሺ 130 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት ይፋ አድርጓል። አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ለእስር ተዳረገው ከቆዩት ከእነዚሁ ሰዎች መካከል 20ሺ 659 የሚሆኑት ስልጠና ወስደው መለቀቃቸውን ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።

ይሁንና 4ሺ 996 የሚሆኑት ሰዎች ከህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ለህግ እንደሚቀርቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።

የመርማሪ ቦርድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሁኔታ በተመለከተ ማክሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያን ያቀረበ ሲሆን፣ መንግስት የፊታችን ሃሙስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርዘም አለመርዘሙን በተመለከተ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ለስድስት ወራት እንዲቆይ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቅርቡ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርጎበት ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል በመንግስት በኩል ፍንጭ መሰጠቱ ይታወሳል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ህዝቡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካለው ጠቀሜታ አንጻር እንዲቀጥል ፍላጎት አሳይቷል ሲሉ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትን የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት አዋጁ ለሰብዓዊ ጥሰት መባባስ ምክንያት ሆኗል በማለት ቅሬታን ሲያቀርቡ መሰንበታቸው የሚታወስ ነው።

እነዚሁ አካላት የኢትዮጵያ መንግስት ከህዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች የሃይል ዕርምጃን እንደ አማራጭ ከመውሰድ ይልቅ ህጋዊ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።

መንግስት በበኩሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያመጣው ለውጥ በሂደት እየታየ መነሳት ወይም አለመነሳቱ ይወሰናል ሲል በቅርቡ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።

ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል ቀጥሎም በአማራ ክልል ከተዛመተው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ከ700 በላይ ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ሲገልጹ ቆየተዋል።

አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ባለሃብቶች በበኩላቸው ለአንድ አመት ያህል በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞና ተግባራዊ ተደርጎ በሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ክፉኛ መጎዳቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትም ባለፈው አንድ አመት ብቻ በአምስት በመቶ ማሽቆልቆሉን የፋይናንስ አካላት በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።