በመገንባት ላይ ያሉና በቀጣይ የሚገነቡ የባቡር መስመሮች ከግንባታ እስከ ማስተዳደር ያለው ስራ ለውጭ ሃገር ኩባንያ እንዲሰጥ መንግስት ወሰነ

ኢሳት (መጋቢት 19 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ መንግስት ያጋጠመውን የፋይናንስ የብድር አቅርቦት ችግር ተከትሎ በመገንባት ላይ ያሉና በቀጣይ የሚገነቡ የባቡር መስመሮች ከግንባታ እስከ ማስተዳደር ያለው ስራ ለውጭ ሃገር ኩባንያ እንዲሰጥ ወሰነ።

በዚሁ አዲስ ስምምነት መሰረትም የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሞጆ-ሃዋሳ-አርባ ምንጭ-ሞያሌ የባቡር መስመር ግንባታ እና አስተዳደርን ለውጭ ሃገር ኩባንያ ለመስጠት የሚያስችል የመግባባቢያ ሰነድ መፈረሙን ሰኞ ይፋ አድርጓል። ኮርፖሬሽኑ የባቡር መስመር ግንባታዎችን ለማከናወን ከተለያዩ አካላት ሲወስድ የቆየው የብድር መጠን ወደ 110 ቢሊዮን ብር አካባቢ መድረሱን ኮርፖሬሽኑ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት መግለፁ ይታወሳል።

መንግስታዊ ድርጅቱ ሲወስድ የቆየው የብድር መጠን ለመንግስት የፋይናንስ ጫናን በማሳደሩና ለዘርፉ ብድር የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ ኮርፖሬሽኑ ለውጭ የግል ኩባንያ እንዲሰጥ ማድረጉ ታውቋል።

መንግስት በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እገነባቸዋለሁ ብሎ ካቀዳቸው በርካታ የባቡር መስመር ግንባታዎች መካከል ግንባታው የተጀመረው የአዋሽ-ወልዲያ- መቀሌ የባቡር መስመር ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።

የተቀሩት ፕሮጄክቶችን ስራ ለማከናወን መንግስት የፋይናንስ የብድር አቅርቦት እጥረት ስላጋጠመው አማራጭ መንገድ ለመፈለግ መገደዱ ተመልክቷል።

በብድር አለመገኘት ምክንያት ግንባታቸው ካልተጀመረው የባቡር መስመሮች ውስጥ የሞጆ-ሃዋሳ-አርባ ምንጭ-ሞያሌ የባቡር  መስመርን በግል ኩባንያ ለማስገንባትና ለማስተዳደር የሚያስችል ስምምነት መፈረሙም ታውቋል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ጌታቸው በትሩ ስምምነቱ ከየትኛው ኩባንያ እንደተፈረመና የገንዘቡን መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ኮርፖሬሽኑ ስሙን መጥቀስ ካልፈለገው ኩባንያ ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት የባቡር መስመሩን በመገንባት ከግንባታ በኋላም የግንባታ ወጪው እስኪመለስ ድረስ የባቡር መስመሩን የማስተዳደር መብት እንዳለው ተገልጿል።

ኩባንያዎቹ ፈቃደኛ ከሆኑ የገነቡትን የባቡር መስመር ለመንግስት ማከራየት የሚችሉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ መንግስት እገነባዋለሁ ብሎ በእቅድ የያዘው ወደ 5ሺ አካባቢ የባቡር መስመር ግንባታ ወደግል ኩባንያ እንዲዛወር ተወስኗል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት በበኩላቸው መንግስት በአስገዳጅነት የተከተለው አማራጭ በባቡር መስመር ግንባታዎቹ ላይ የዋጋ ንረት ሊያስከትል እንደሚችልና የአገልግሎቱ  ክፍያም ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው የባቡር መስመር የዋጋ ተመን በማን እንደሚወሰን የስምምነት ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ በከፊል የተገነባውን ቀላል የባቡር መስመር ግንባታ ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ሊከናወኑ የታሰቡ ፕሮጄክቶችን ለማገዝ የቻይና ኩባንያዎች ፍላጎት ማሳየታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ የቻይና መንግስትም ብድር ሲሰጥ መቆየቱ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ አበዳሪ አካላት የሚወስደው ብድር መጠኑ ከፍ እያለ መምጣቱን ተከትሎ የአለም ባንክ በብድር አወሳሰዱ ላይ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ነሃሴ 2015 አም ድረስ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የብድር መጠን 36 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ደርሶ እንደነበር ይፋ ተደርጓል።

ይኸው የብድር መጠን እየጨመረ መምጣቱ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩንና ለመንግስት ፈታኝ ሆኖ መቀጠሉን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።