መጋቢት 13: 2009)
በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ሳምንት ጊዜ የቀጠለው የነዳጅ እጥረት በነዋሪዎች ላይ ማህበራዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጹ።
በተለይ የህዝብ ትራንስፖርት ተጠቅመው የተለያዩ ጉዳዮች የሚያከናውኑ ነዋሪዎች የነዳጅ እጥረቱ ለሁለተኛ ሳምንት በመቀጠሉ ምክንያት ለዘርፉ ብዙ ችግር መዳረጋቸውን አስታወቀዋል።
በመዲናይቱ የሚገኙ የተሽከርካሪ ባለሃብቶች በበኩላቸው ነዳጅ ለማግኘት በነዳጅ ማደያ አካባቢዎች ለማደር መገደዳቸውን ጭምር ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ለመንግስት ስራና ለግል ጉዳዩች ለመንቀሳቀስ የህዝብ ትራንስፖርት የሚጠቀሙ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በነዳጅ እጥረቱ ሳቢያ ለሰዓታት በመንገድ ላይ ትራንስፖርት ለማግኘት መንገላታታቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በበኩሉ በነዳጅ አቅርቦት ላይ የተፈጠረ ምንም ችግር የለም በማለት ከጎረቤት ሱዳንና ጅቡቲ ወደብ ነዳጅ በበቂ ሁኔታ መግባቱን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በሃገሪቱ የነዳጅ ስርጭትን ሃላፊነት የሚመለከተው የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ችግሩ የተፈጠረው ለረጅም ጊዜ ተቋጥሮ የነበረው ቤንዚን ከኢታኖል ጋር የማደባለቅ ስራ እንደገና በመጀመሩ እንደሆነ ምላሹን ሰጥቷል።
በነዳጅ እጥረቱ ለችግር መዳረጋቸውን የሚናገሩት ተጠቃሚዎች በበኩላቸው ነዳጅ በሃገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ አለ እየተባልን የምናየው ነገር አለመኖሩን ጥያቄ አሳድሮብናል ሲሉ አስረድተዋል። በተለያዩ የመዲናይቱ ጎዳናዎች በርካታ ነዋሪዎች ትራንስፖርት ለመጠበቅ ሲንገላቱ ተስተውለዋል።