ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች የያዙትን ገንዘብና ጌጣጌጥ ጭምር እንዲያስመዘግቡ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ሆነ

መጋቢት 13: 2009)

የውጭ ምንዛሪ ዝውውርን ለመቆጣጠር ሲባል ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች የያዙትን ገንዘብና ጌጣጌጥ ጭምር እንዲያስመዘግቡ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ሆነ።

ከዚህ በፊት ከተለያዩ ሃገራት የአየር ትራንስፖርት ተጠቅመው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች 24 ሰዓት እስካልሞላቸው ድረስ የያዙትን ገንዘብም ሆነ ጌጣጌጥ ማስመዝገብ እንደማይጠበቅባቸው ታውቋል።

ይሁንና በአዲሱ መመሪያ መሰረት ማንኛውም ተጓዥ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ በእጁ የሚገኙ ገንዘቦችን እንዲሁም ጌጣጌጦችን እንዲያስመዘግብ መደረጉን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ገልጸዋል።

ቀድሞ የነበረው አሰራር ሃብትና የውጭ ምንዛሪ ለማሸሽ መንገድ ፈጥሯል ያለው ባለስልጣኑ፣ ሃገሪቱን ተጠቅመው ወደ ሌላ ሃገር የሚጓዙ መንገደኞች ሁሉ መመሪያው እንደሚመለከታቸው አስታውቀዋል።

ባለፈው አመት ብቻ አራት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ዜጋ በሆኑ መንገደኞች ሊወጣ ሲል መያዙን የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።

በመስሪያ ቤቱ የመንገደኞች ጉዳይ ምክትል ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ በየነ ከተያዘው ገንዘብ ውስጥ መንግስት የወረሰው መኖሩን ተናግረዋል። ይሁንና ሃላፊው የተወረሰውን ገንዘብ መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታም በተያዘው አመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራቶች ኢትዮጵያውያን መንገደኞች በ100 ሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ይዘው ሊወጡ ሲሉ መያዛቸውን ሃላፊው አክለው አስረደተዋል።

አቶ ሙሉጌታ አዲሱ መመሪያ የውጭ ምንዛሪ ከሃገር መውጣት ሊያስቀር እንደሚችል ቢገልጹም የውጭ ዜጋም ሆነ ኢትዮጵያ ምን ያህል ገንዘብ ይዞ መንቀሳቀስ እንዳለበት የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም። የመንግስት ባለስልጣናት በቅርቡ በህገወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ተግባራዊ እንደሚደረግ መግለጻቸው ይታወሳል።

መንግስት ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ ጀምሮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳጋጠመውና ድርጊቱ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን የአለም ባንክና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ሲገልፁ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ውጭ ንግድ ማሽቆልቆል፣ የብድር ክምችትና ማነስና መንግስት በብቸኝነት እያከናወነ ያለው የልማት ፕሮጄክቶች ግንባታ በሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪና የፋይናንስ አቅም ላይ ጫና ማሳደሩን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።

የአለም ባንክ በበኩሉ መንግስት ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የውጭ ብድርን ከመቆጣጠር በተጨማሪ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን ማድረግ እንዳለበት ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ብር ከዶላር ጋር ያለው የምንዛሪ መጠንም መቀነስ እንዳለበት ባንኩ ሃሳብን ቢያቀርብም የመንግስት ባለስጣናት የአለም ባንክ ያቀረበው ሃሳብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል በማለት ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ይሁንና፣ ብር ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅምና ምንዛሪ በየዕለቱ መዋዠቅን እያሳየ እንደሚገኝ አመልክቷል።

ተባብሶ የቀጠለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ በውጭ ንግድ ዘርፍ የሚደረገው ጥረትም ሊሳካ ባለመቻሉ፣ ላኪዎች በጠ/ሚ/ሩ ቢሮ ለስብሰባ መጠራታቸም ተመልክቷል።

በ2009 የበጀት ግማሽ አመት ከውጭ ንግድ ይገኛል ተብሎ የተጠበቀው የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ የተገኘው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም ከአምናው ገቢም ያነስ ሆኖ ተመዝግቧል።