ኢሳት ( መጋቢት 7 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ላይ በደረሰው አደጋ የሃይማኖት ተቋማትና የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫ በማውጣት ሃዘናቸውን ገለጹ።
በውጭ አገር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በምክትል ዋና ጸሃፊው በአቡኑ ሚካዔል ስም ባወጣው መግለጫ፣ ለሞቱን ሃዘኑን ገልጾ፣ ለቤተሰብ መጽናናንትን ተመኝቷል። ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሞቱትን በጸሎት እንዲያስቡና ለሟች ቤተሰቦች ደግሞ ድጋፍን እንድያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ የአፋር ህዝብ ፓርቲና የሲዳማ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት በጋራ የመሰረቱት የኢትዮጵያ ሃጋራዊ ንቅናቄም መግለጫ በማውጣት አጋርነቱን አሳይቷል።
ለአደጋው መንግስትን ተጠያቂ ያደረገው የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ፣ ይህ የመከራ ዘመን እንዲያበቃ ኢትዮጵያውያን በጋራ ክንዳቸውን እንዲያስተባብሩ ጠይቆ፣ በርሱ በኩል ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለቀመንበሩ ዶ/ር ዲማ ነገዎን በመጥቀስ በመግለጫው አስፍሯል። በመጨረሻ ለሰለባዎቹ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቷል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ እንዲሁም አረና እና የደቡብ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶችን ያቀፈውን በሃገር ቤት የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ ሃዘኑን በመግለጽ ለሟች ቤተሰቦች ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
“የቆሻሻው ተራራ የገነባው ራሱ መንግስት በመሆኑ ለአደጋው ተጠያቅው መንግስት ነው” ያለው የመድረክ መግለጫ፣ ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት መንግስት የመከላከል ስራ እንዲሰራና የሰለባዎችን ቤተሰቦችም እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል።