የጎንደር ፖሊስ አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ አባል ታሰሩ

ኢሳት (መጋቢት 7 ፥ 2009)

የጎንደር ከተማ ፖሊስ አዛዥ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል ታሰሩ። የጎንደር ከተማ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኮማንደር አሰፋ ሹሜ ረቡዕ መጋቢት 6 ፥ 2009 መታሰራቸው ቢረጋገጥም፣ ስለታሰሩበት ምክንያት የታወቀ ነገር የለም።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ ኮማንድ ፖስት ስር መቀጠላቸው የተገለጸው ኮማንደር አሰፋ ሹሜ፣ ረቡዕ ከስራና ስልጣናቸው ተነስተው ወደ እስር ቤት ተወስደዋል። በተመሳሳይ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረም፣ ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል።

ለፖሊስ አዛዡ መታሰርና ለከንቲባው ከስልጣን መነሳት ምክንያት የሆነው ጉዳይ በግልፅ ባይታወቅም፣ በጎንደር ውስጥ መሳሪያ ያየዙ ሃይሎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ሲገለጽ፣ እያደፈጡ ጥቃት በመሰንዘር ላይ መሆናቸውም ይታወቃል። በሳምንቱ መጀመሪያ በጎንደር የተለያዩ ስፍራዎች የአርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎች የደፈጣ ጥቃት በመፈጸም ጉዳት ማድረሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በአማራ ክልል በቀጠለው ግምገማ 16 ከፍተኛ አማራሮች ከስልጣናቸው ሲነሱ፣ አስራ አንዱ ከደረጃቸው ዝቅ በለው እንዲሰሩ መወሰኑን የክልሉ ገዢ ፓርቲ ብአዴን/ኢህአዴግ አስታውቋል።

በዞን ደረጃ ከሚገኙ 494 አመራሮች 80 የሚሆኑት መሻራቸውም ተመልክቷል። በዝቅተኛ ዕርከን ላይ ከሚገኙት 6ሺህ ያህል አመራሮች 995 ቱ ከስልጣናቸው መሻራቸውም ከድርጅቱ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።