የአርበኞች ግንቦት7 ታጋዮች ተጨማሪ ጥቃት መፈጸማቸውን ገለጹ

መጋቢት ፯ (ሰባት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ታጋዮቹ ለኢሳት እንደተናገሩት በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች መጋቢት 5 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን፣ የዚሁ የዘመቻ አካል የሆነ ጥቃት በአምባጊዮርጊስ ከተማ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። ከምሽቱ 6 ሰአት አካባቢ በተፈጸመው ጥቃት የወረዳው እስር ቤት ከጥቅም ውጭ መሆኑን ተናግረዋል።
አምባጊዮርጊስ የመከላከያ ሰራዊት እና የሚሊሺያ አባላት በብዛት የሚገኙበት ከተማ ሆኖ ሳለ እንዴት ጥቃቱን ለመፈጸም ቻላችሁ በሚል ጥቃቱን ላደረሰው ግብረሃይል አመራር ላቀረብነው ጥያቄ፣ በአካባቢው ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳለ ብናውቅም፣ ህዝብ እየመራ መንገድ ስላሳየን በሰላም ገብተን ስራችንን ሰርተን ለመውጣት ችለናል ብሎአል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሰሜን ጎንደር ዞን የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር አሰፋ ሹሜ ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል። ኮማንደሩ በአካባቢው በታጋዮች የሚደርሰውን ጥቃት ለመቆጣጠር አልቻለም በሚል ተይዞ መታሰሩ ታውቋል።