መጋቢት ፮ (ስድስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ቆሸ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የደረሰውን አሰቃቂ አደጋ ተከትሎ፣ ሟቾችን በፍጥነት ለማውጣት ባለመቻሉ የአስከሬኑ ሽታ ከቆሻሻ ሽታው ጋር ተደማምሮ ፍለጋውን አስቸጋሪ አድርጎታል። የኢህአዴግ አገዛዝ ሁለት ስካቫተር እና 3 አምቡላንስ መኪኖችን ብቻ በማቅረቡ፣ ፍለጋው እንዲጓተትና በህይወት የተረፉ ሰዎችን የማፈላለጉ ስራ እንዲስተጓጎል እያደረገ ነው የሚል ትችት ከቀረበበት በሁዋላ፣ ትናንት ሁለት ተጨማሪ ስካቫተር መኪኖችን አቅርቧል። የአይን ዕማኞች እንደሚሉት አስከሬን ለሚፈልጉ ወጣቶች ምግብ ለማድረስ የሞከሩ ሰዎች ወደ አካባቢው ለመሄድ ቢሞክሩም በፖሊሶች ተከልክለዋል።
ሁኔታው እጅግ አሳዛኝ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ አሁንም በርካታ ያልወጣ አስከሬን መኖሩን ገልጸዋል። አሁን በመንግስት የሚነገረው ቁጥር ትክክል አይደለም የሚሉት ነዋሪዎች፣ ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር በብዙ መቶዎች ይቆጠራል ይላሉ።እንዲሁም ቆሻሻው አሁንም ዳግም ይናዳል በሚል የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት ላይ ወድቀዋል።
ዘወትር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ድምጻቸውን በማሰማት የሚታወቁት የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል ወ/ሮ አና ጎሜዝ በበኩላቸው በአዲስ አበባ የደረሰውን እልቂት አውግዘው፣ የህብረቱ ፓርላማ በዚህ በተበላሸ ስርዓት ላይ ከቃል ያለፈ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።