ህዳር 25 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በትራንስፎርሜሽን እና እድገት ስም የመለስ መንግስት ባለፉት 10 አመታት ብቻ ከቻይናና ከህንድ መንግስታት ከ 25 ቢሊዮን ዶላር በላይ መበደሩን መረጃዎች አመልክተል። ይህን ኢትዮጵያ ከፍተኛ በሆነ ብድር ከተዘፈቁ አገሮች ተርታ እንዳስመደባት ታውቋል።
ለኢትዮጵያ ከፍተኛውን ብድር ከሰጡት የቻይና ባንኮች መካከል ፣ ኤግዚም ባንክ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ አበድሯል።
የባንኩ ምክትል ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሚስተር ዙ ሆንግጂን ኢትዮጵያ ተጨማሪ ብድር እንድታገኝ ለማስቻል በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር መገናኘታቸው ታውቋል።
ከምእራባዊያን የሚሰጠው ብድር እያነሰ መምጣት ያሳሰባቸው አቶ መለስ ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፊታቸውን ወደ ቻይና፣ ህንድና ደቡብ ኮሪያ አዙረዋል።
የቻይና ኩባንያዎች እስከዛሬ ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር መስጠታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። የህንድ ኩባንያዎችም በተመሳሳይ ለኢትዮጵያ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ሰጥተዋል።
ሰሜን ኮሪያና ጀፓንም ከ2 ቢሊዮን ዶላር ማበደራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በመበደር የመለስ መንግስት ተወዳዳሪ አልተገኘለትም።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ አገራዊ ምርቱ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደማይበልጥ ይታወቃል።
ከቻይናና ህንድ በመደር ሁለት ጉዳት እንዳለው የሚናገሩት ባለሙያዎች፣ የወለድ መጠን መብዛት እና የእዳ ቅነሳ ለማግኘት አለመቻልን በምክንያትነት ያቀርባሉ።
ከፍተኛ ሙስና በሚፈጸምባት ኢትዮጵያ የውጭ ብድር ማብዛት አገሪቱ በማትወጣው አዘቅት ውስጥ እንደምትገባና የቻይናና የህንድ የእጅ አዙር ቅኝ ተገዢ እንደምትሆንም ያስጠነቅቃሉ።
የምእራብ የገንዘብ ተቋማትና መንግስታት ከ5 አመታት በፊት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የእዳ ስረዛ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያን እጅግ ከፍተኛ ሙስና ከተንሰራፋባቸው አገሮች ተርታ መድቧታል።
ትራንስፓረንሲ ኢንትርናሽናል እንደሚለው ከፍተና የሆነ የውጭ እርደታ የሚያገኙ አገሮች፣ ከአስሩ እጅ አንዱን ብቻ አስቀርተው 9ኙን በሙስና ወደ ውጭ አገር የሚያስወጡት ከሆነ ብድር መበደሩ ዘላቂ የሆነ ጉዳት ያመጣል።