በትግራይ ክልል ፕሬዚደንት መዘግየት የተስተጓጎለው የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ኮሚሽን ስብሰባ በመቀሌ ተጀመረ

ኢሳት (የካቲት 10 ፥ 2009)

በትግራይ ክልል ፕሬዚደንት መዘግየት ለአንድ ቀን የተስተጓጎለው የኢትይጵያና የሱዳን የድንበር ኮሚሽን ስብሰባ መቀሌ ላይ ተጀመረ። የአማራ ክልል ፕሬዚደንት እና ምክትል ፕሬዚደንቱ ያልተገኙ ሲሆን፣ የቤኒሻንጉል ክልል ፕሬዚደንት እንዲሁም የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ተሳታፊ መሆናቸው ተመልክቷል።

የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት አቶ አባይ ወልዱ ልዑካኑ ትግራይ ሲገቡ፣ እርሳቸው አዲስ አበባ ስለነበሩ ስብሰባው ለአንድ ቀን እንዲራዘም ምክንያት ሆኗል።

የአማራ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በስብሰባው ያልተገኙት በቤተሰብ ሃዘን ሳቢያ መሆኑ ሲገለፅ፣ ርሳቸውን መተካት የነበረባቸው ምክትል ፕሬዚደንቱ አቶ ብናልፍ አንዷለም ያልተገኙበት ምክንያት ግልጽ አልሆነም። አማራ ክልል በዝቅተኛ ባለስልጣናት መወከሉም ታውቋል።

የቤኒሻንጉል ክልል ፕሬዚደንት ከመነሻው ጀምሮ በሂደቱ ውስጥ የነበሩ ቢሆንም፣ የአማራና የትግራይ ክልል ፕሬዚደንቶች አለመገኘታቸው ለሂደቱ መጓተት ምክንያት ሆኗል።

ለሁለት ቀናት ይካሄዳል ተብሎ የተስተጓጎለውና በመቀሌ ሰማዕታት አዳራሽ አርብ ተጀምሮ አርብ የተጠናቀቀው የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ኮሚሽን ስብሰባ አባላት ማምሻውን በፕላኔት ሆቴል የዕራት ግብዣ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ለሱዳን ልዑካን የማር ስጦታ እንደተበረከተላቸው መረዳት ተችሏል።

መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ስብሰባው ቅዳሜ የካቲት 11 እንደሚቀጥል ቢናገሩም፣ ስብሰባ መጠናቀቁን ኢሳት ከመቀሌ ምንጮች አረጋግጧል።

የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ጉዳይ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ትኩረት የሚስብና በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚከታተሉት ሲሆን፣ የሁለቱ ሃገር ጉዳይ ከፌዴራል መንግስቱ እጅ ወጥቶ በክልሎች ደረጃ የሚታይበት ህጋዊ ምክንያት መሰረት ግልፅ ሳይሆን ቀጥሏል።

እንግዶቻቸው ወደርሳቸው መቀመጫ መቀሌ ሲገቡ፣ እርሳቸው ደግሞ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት የትግራይ ክልል ፕሬዚደንትና የህወሃት ሊቀመንበር አቶ አባይ ወልዱ፣ አዲስ አበባ ስለተጓጓዙበትም ሆነ ስለቆዩበት ጉዳይ የታወቅ ነገር የለም።