በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ባለፉት 15 አመታት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 10 ፥ 2009)

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ባለፉት 15 አመታት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ሃገሪቱ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን አንድ ተቋም በጉዳዩ ዙሪያ ያካሄደውን ጥናት ዋቢ በማድረግ አርብ ይፋ አደረገ።

እንደፈረጆቹ አቆጣጠር እስከ 2015 አም ድረስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የመጡ ዜጎች ቁጥር 2.1 ሚሊዮን ሲሆን፣ ከዚሁ ቁጥር መካከል 222ሺ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ፒው (PEW) የተሰኘ የምርምር ማዕከል በወጣው ሪፖርት ገልጿል።

ናይጀሪያ ግንባር ቀደም በመሆን ወደ 327 ሺ ዜጎቿ ወደ አሜሪካ የገቡ ሲሆን፣ ግብፅ በ 192 ሺ ከኢትዮጵያ በመቀጠል በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ወደ አሜሪካ የሚገቡ አፍሪካውያን ቁጥር ባለፉት 15 አመታት በእጥፍ ቢያድግም፣ አሁንም ድረስ የአፍሪካዊያን ቁጥር ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን የማዕከሉ ሃላፊዎች ለቪኦኤ እንግሊዝኛ ክፍል አስረድተዋል።

በዚሁ ጥናት ተሳታፊ የሆኑት ሞኒካ አንደርሰን እንደፈረንጅቹ አቆጣጠር በ1980 በአሜሪካ የሚኖሩ አፍሪካውያን ድርሻ አንድ በመቶ ብቻ እንደነበር አውስተው ቁጥሩ በ2015 በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አስታውቀዋል።

በጥናቱ የተመለከተው ቁጥር ወደ አሜሪካ የተጓዙት እንጂ በሃገሪቱ የተወለዱትን የማያካትት ሲሆን፣ አብዛኞቹ አፍሪካውያን በቴክሳስ፣ ካሊፎርንያ፣ ኒው ዮርክና ሜሪላንድ ግዛቶች ዙሪያ እንደሚኖሩ ሞኒካ ገልጸዋል። በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት መካከል በርካታ ሃኪሞች፣ የምህንድስና ባለሟያዎች እንደሚገኙበት አንደርሰን አክለው አስረድተዋል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከ 2013 አም ድረስ 38 በመቶ የሚሆኑት የሰብ ሰሃራ አፍሪካ ሃገራት ነዋሪዎች የባችለር ዲግሪን የያዙ ሲሆን፣ የተቀረሩ  ስደተኞች ቁጥር 28 በመቶ ብቻ የሚገኙት ዲግሪውን እንደያዙ በሪፖርቱ ሰፍሯል።

ጋና፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሶማሊያ ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ደረጃን ለመያዝ በቅተዋል።

በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ጭማሪን ያሳይ ወይም ባለበት ይቆይ ይሆን የሚለው ጉዳይ በሂደት የሚታይ ሁኔታ መሆኑን ባለሙያዎች ለዜና አውታሩ አስረድተዋል።