በዚምባብዌ ፍርድ ቤት ከቀረቡት 56 ኢትዮጵያውያን 8ቱ ራሳቸውን ስተው ሆስፒታል ገቡ

ኢሳት (የካቲት 10 ፥ 2009)

በህገወጥ መንገድ ወደ ዚምባቢዌ ገብታችኋል ተብለው ለእስር ከተዳረጉ 56 ኢትዮጵያውያን መካከል 8ቱ ፍርድ ቤት በቀረቡ ጊዜ ራሳቸውን ስተው ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን የዚምባብዌ ባለስልጣናት አርብ ገለጹ።

ስደተኛ ኢትዮጵውያኑ የተመሰረተባቸውን ክስ ለመስማት በማታቤላንድ ግዛት ስር በምትገኘው የግዋንዳ ከተማ ቢገኙም ሳምንት በችሎቱ ፊት ራሳቸውን ስተው እንደወደቁና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የዚምባብዌ ፖሊስ ለመገኛኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያውያኑ በፍርድ ቤቱ በተገኙ ጊዜ ለቀናት ምግብና ውሃ ሳይቀርብላቸው በእስር ቤት መቆየታቸውን መናገር ጀምረው እንደነበር ክሮኒክል የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ላይ ነበሩ የተባሉት ኢትዮጵያውያን አቤቱታቸውን ለችሎቱ ማቅረብ በጀመሩ ጊዜ ስምንቱ ራሳቸውን ስተው እንደወደቁና ድርጊቱ በፍርድ ቤት ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሮ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።

የግዋንዳ ከተማ ሆስፒታል ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ቸርጊ ቺምበርንግዊ ሳምንቱ ኢትዮጵያውያን ከምግብና ፈሳሽ እጥረት የተነሳ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበርና የህክምና ባለሙያዎች የህክምና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ለጋዜጣው አስረድተዋል።

በስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ላይ የደረሰውን ይህንኑ ክስተት ተከትሎም የከተማዋ ፍርድ ቤት 56ቱ ኢትዮጵያውያን አሁን ካሉበት መደበኛ እስር ቤት በኢሚግሬሽን ተቋም ስር በሚገኝ ማቆያ እንዲቆዩ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ታውቋል።

ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ሲያጓጉዝ ነበር የተባለ አንድ የሃገሪቱ ዜጋ በ500 ዶላር ወይም በ60 ቀን እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኒን የሰጠ ሲሆን፣ ስደተኞቹ ዕድሚያቸው ከ17 እስከ 27 አመት መካከል መሆኑ ተመልክቷል።

ከቅርብ ጊዜ ዜምባብዌን ጨምሮ ወደተለያዩ ደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (IOM) መረጃ ያመለክታል።

በአሁኑ ወቅት በዛምቢያ፣ ዚምባብዌ፣ ታንዛኒያና እና ማላዊ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በየመንና ሊቢያ እንዲሁም በጎረቤት ሱዳን በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።