ዜና (የካቲት 2 ፥ 2009)
በደቡብ እና ደቡባዊ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተያዘው ወር መጣል የነበረበት የበልግ ዝናብ ባለመጀመሩ ምክንያት የድርቅ መባባስ ስጋት መኖሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በበኩሉ ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ከተጋለጡ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 2.5 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑት በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።
ካለፈው ሃምሌ ወር ጀመሮ በአራት ክልሎች የተከሰተው የድርቅ አደጋ በኦሮሚያ ክልል መጠነ ሰፊ የሆነ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በተለይ በተያዘው ወር መጣል የነበረበትን የበልግ ዝናብ ባለመጀመሩ ምክንያት በደቡብ እና ደቡባዊ ምስራቅ የሃገሪቱ አካባቢዎች ድርቁ እየበረታ ሊሄድ እንደሚችል ተመድ አስታውቋል። በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች ችግሩን በመረዳት በአጭር ጊዜ ሊደርስ በሚችሉ ሰብሎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል።
የበልግ የዝናብ ወቅት በሚጠበቀው መጠን ባለመሆኑ ምክንያት በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብ እና የሶማሊ ክልሎች ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች ለከፋ የድርቅ አደጋ ይጋለጣሉ ተብሎ ተሰግቷል።
አለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ በሚፈለገው ጊዜና መጠን ወደ ሃገሪቱ መግባት ካልጀመረ የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል በማሰባሰብ ላይ ናቸው።
የመንግስት ባለስልጣናት በአራቱ ክልሎች ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል በክልልና በፌዴራል ደርጃ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን እንደገለጹ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በበኩሉ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ከተጋለጡ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 2.5 አካባቢ የሚሆኑት በክልሉ ያሉ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች መሆናቸውን አስታውቋል።
የክልሉ የአደጋ መከላከል ኮሚሽን በዚሁ የድርቅ አደጋ ዘጠን ዞኖች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።
ቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌ፣ ምስራቅና፣ ምዕራብ አርሲ አዲሱ የድርቅ አደጋ የከፋ ችግር እየደረሰባቸው ካሉ ዞኖች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸው ተመልክቷል።
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ለእርዳታ ለተጋለጡ ሰዎች የምግብ ድጋፍ መቅረብ መጀመሩን የክልሉ ባለስልጣናት ይገልጿሉ።
ተመድ ድርቁን ለመከላከል ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ በቅርቡ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ባለፈው አመት በተመሳሳይ መልኩ በስድስት ክልሎች 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለምግብ ድጋፍ አጋልጦ የነበረው የድርቅ ክስተት ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ሳያገኝ አዲስ የድርቅ አደጋ መከሰቱ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።