የቀድሞ የሶማሊያ ጠ/ሚኒስትር አብዱላሂ ሞሃመድ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ሆነው ተመረጡ

ዜና (የካቲት 2 ፥ 2009)

የቀድሞ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላሂ ሞሃመድ የሃገሪቱ አዲሱ ፕሬዚደንት ሆነው ተመረጡ።

ረቡዕ ከፍተኛ ጥበቃ በተደረገበት ሁኔታ ሞቃዲሾ በሚገኝ የአየር ማረፊያ በተካሄደው በዚሁ የፓርላማ አባላት ድምፅ የመስጠት ሂደት ፕሬዚደንት አብዱላሂ 184 ድምፅ በማግኘት ለድል መብቃታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

20 የሚሆኑ ተፎካካሪዎች ለውድድር ቀርበው በነበሩት በዚሁ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ የነበሩት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ 97 ድምፅን ብቻ በማግኘታቸው ተሸናፊ ሆነዋል።

ኢትዮጵያ የቀድሞን ተሸናፊ ፕሬዚደንት በከፍተኛ ሁኔታ በመደገፏ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚደንት ድል እንዲቀናቸው አስተዋጽዖ ማድረጉን ደግሞ ቢቢሲ በጉዳዩ ዙሪያ በቀረበው ዘገባ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ተሸናፊው ሃሰን ሼክ ሞሃመድ በስልጣን እንዲቆዩ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ ብትቆይም የሃገሪቱ የፓርላማ አባላት በዚሁ ምክንያት ፕሬዚደንት አብዱላሂን ለመምረጥ ፍላጎት ማሳየታቸው ተነግሯል።

ረቡዕ የተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ በሰላም እንዲከናወን ለማድረግ በመዲናዋ ሞቃዲሾ በረራዎች የተሰረዙ ሲሆን፣ ዋና ዋና ጎዳናዎችም ለተሽከርካሪ ዝግ ሆነው መዋላቸውን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።

የወተት ተዋፅዖ በመውደዳቸው በጣሊያንኛ ቋንቋ ፋርማጆ ወይም ቺስ በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት የሶማሊያው ፕሬዚደንት አብዱላሂ ሞሃመድ የአሜሪካ ጥምር ዜግነት እንዳላቸው ቢቢሲ ዘግቧል።

በዚሁ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ሆነው ከቀረቡት 20ዎቹ እጩዎች መካከል 16ቱ የጥምር ዜግነት ያላቸው ሲሆን፣ ዘጠኙ አሜሪካዊ መሆናቸውንም ለመረዳት ተችሏል። የተቀሩት ደግሞ አራቱ የብሪታኒያ ሶስቱ የካናዳ ዜግነት እንዳላቸው ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

ፕሬዚደንታዊ ተፎካካሪዎቹ የፓርላማ አባላትን ድምፅ ለማግኘት ሲሉ እስከ 30ሺ ዶላር ድረስ ይከፍሉ እንደነበርም ከሃገሪቱ የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።

ተሸናፊው የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዚደንት ውጤቱን በመቀበል ለአዲሱ ፕሬዚደንት መልካም የስራ ጊዜን ቢመኙም ፕሬዚደንታዊ ተፎካካሪዎቹ ድምፅ ለማግኘት ሲባል በተከፈለ ገንዘብ ዙሪያ ዕርስ በርሳቸው መወነጃጀላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

የአዲሱ ፕሬዚደንት መመረጥን ተከትሎ በርካታ ሰዎች በመዲናይቱ ሞቃዲሾ አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

ፕሬዚደንት አብዱላሂ ሞሃመድ ፋርማጆ ላለፉት 25 አመታት ማዕከላዊ መንግስት ያለነበራትን ሶማሊያ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንድታገኝ ብዙ ስራዎች እንደሚጠብቃቸውና ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጉትንም ግንኙነት አዲስ አካሄድ ሊኖረው እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።