ህዳር 23 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአማራ ክልል መምህራን ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ መንግስቱ አህመዴ፣ ናዝሬት በተካሄደው አገር አቀፍ የመምህራን ማህበር ጉባኤ ላይ ስብሰባ ረግጦ ወጥቷል ተብሎ ነው
እስካሁን ድረስ ይፋ ባይሆንም፣ በመንግስት ግፊት የአገር አቀፉ የመምህራን ማህበር ግለሰቡን ከሀላፊነት አግደዋቸዋል።
ይሁን እንጅ መምህር መንግስቱ በክልሉ መምህራን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያላቸው በመሆኑ መንግስት እገዳውን በይፋ ለመምህራን ለማስታወቅ አልደፈረም።
መምህር መንግስቱ በአገር አቀፉ የመምህራን ማህበር ጉበኤ ላይ የመምህራንን የደሞዝ ጭማሪ፣ የደረጃ እድገትንና የማስተማርና ሀሳብን የመግለጽ፣ ከሁሉም በላይመምህራን ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ እንዲሆኑ፣ በሰለማዊ ሰልፍ ሳይቀር መብታቸውን እንዲጠይቁ ሊፈቀድላቸው ይገባል የሚል ሀሳብ መሰንዘራቸው ታውቋል።
የመምህራኑ ጥያቄዎች በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ውስጥ እንዲፈቱ ጉባኤው ውሳኔ እንዲያሳልፍ የጠየቁት ሊቀመንበሩ፣ የገዢው ፓርቲ አባል የሆኑት የጉባኤው መሪ ጥያቄያቸውን ውድቅ ሲያደርጉ፣ መምህር መንግስቱ ጉበኤውን ረግጠው ወጥተዋል።
የእርሳቸውን ከጉባኤው መውጣት ተከትሎ ከእርሳቸው ጋር አብረው የመጡ ሌሎች ልኡካኖችም ስብሰባውን ረግጠው ለመውጣት ተገደዋል።
መንግስት በሊቀመንበሩ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ቢከፍትም እስካሁን ድረስ የመምህራንን ድጋፍ ሊያገኝ እለቻለም።
መምህር መንግስቱ መምህራን አድማ እንዲያደርጉ እያበረታቱ ነው በሚል ሰበብ ለእስር ሳይዳረጉ እንደማይቀርም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የመለስ መንግስት አንጋፋውን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርን ካፈረሰ በሁዋላ፣ ለመምህራን መብት የሚቆረቆር ጠንካራ ድርጅት እንዳይወጣ ማድረጉ ይታወቃል።