ጥር ፲ ( አሥር )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አብዛኛው የጎንደር ህዝብ በአካባቢው የሚፈጸመውን ከፍተኛ የመብት ጥሰት በመቃወም የዘንድሮው የከተራ በአል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በቀዘቀዘ ስሜት መካሄዱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።ከዚህ በፊት የነበሩት ስርዓቶች በአብዛኛው የቀሩ ሲሆን፣ ታቦታቱ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ፖሊሶችና በተወሰኑ ምዕመናን ታጅበው እንዲወጡ ተደርጓል። በገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ጫና የበአሉ ስነሰርዓት እንዲከበር ቢደረግም፣ ወጣቶች በቡድን በመሆን የተቃውሞ ድምጾችን ሲያሰሙ እንደነበር የአይን እማኞች ተናግረዋል።
ባለፉት አመታት የጎንደርን የጥምቀት በአል ለመከታተል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ የሚጎርፉ ቢሆንም በዘንድሮው በአል ላይ ግን አልተገኙም። ከበአሉ አንድቀን ቀደም ብሎ አርማ የሌለበትን የኢትዮጵያን ሰንደቃላማ ሲዘረጉ የታዩ ወጣቶች በፖሊሶች ተይዘው ታስረዋል።
ከበአሉ አከባበር ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ፍተሻ ሲደረግ መዋሉን፣ የፖሊስ ጥበቃውም ከፍተኛ እንደነበር ወኪሎቻችን ገልጸዋል።