ኢሳት (ታህሳስ 28 ፥ 2009)
“ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ” በሚል በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደ ህዝባዊ ስብሰባ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር የቆሙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ድርጅቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀረበ። በኢትዮጵያ ለለውጥ የሚታገሉ ሃይሎችም ተባብረው እንዲሰሩም በዚሁ መድረክ ተጠይቀዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚደንት ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ” በኢትዮጵያ መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚሰራ ድርጅት መሆኑን በዚሁ ህዝባዊ መድረክ አብራርተዋል።
ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ እንዲከበር ይህም የመብላት የመጠጣት፣ የመማር፣ የጤና ጥበቃ የማግኘት፣ የጾታ ዕኩልነት ወዘተ እንደሚጨምር ለተሰብሳቢው ያስታወሱት ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ እንዲሁም የሲቪክ ተቋማት ለዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸውን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተዋል። የሴቶች የመምህራን፣ የነጋዴዎች ወዘተ ማህበራት የዴሞክራሲ፣ የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ሊደገፉ እንደሚገባ አሳስበዋል። ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትና መረጃ የማግኘት መብት ለዴሞክራሲ ስርዓት ያላቸው አስተዋጽዖ በመዘርዘር አጠቃላይ መብቶች በኢትዮጵያ እንዲከበሩ “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ” የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲደግፉና እንዲቀላቀሉም ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የመኢአድ ም/ፕሬዜደንት እንዲሁም የቅንጅት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ አባይነህ ብርሃኑ፣ የተቃውሞ ሃይላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተናጠል የሚደረግ ሩጫ ውጤቱ ውድቀት እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በዚሁ “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ” በጠራው መድረክ ሌላው ተናጋሪ የሆኑት የቅንጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት ወ/ሮ ንግስት ገ/ህይወት የኢትዮጵያን ህዝብ ደግነትና ሩህሩህነት በማስታወስ ከዚህ ህዝባችን የትብብርን አስፈላጊነት ልንረዳና ልንከተለው ይገባል ሲሉ የአቶ አባይነህ ብርሃኑን ሃሳብ አጠናክረዋል። በትግሉ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ አስፈላጊነት ስለመሆኑም አጽንዖት ሰጥተዋል።
ከተሰብሳቢው የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል። በተለይ ለዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት አንድ ተሰብሳቢ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲታገል እርስዎ የት ነበሩ በሚል ላቀረቡት ጥያቄ ዶ/ር ታዬ ምላሽ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርብ ሲከታተሉ መቆየታቸውን በተለይም እየተካሄደ ያለው ጭቆና ሲያስጨንቃቸው መቆየቱን አስታውሰው፣ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ በዚሁ ረገድ የሚኖረውን አስተዋጽዖ ጠቅሰዋል። ለሃገሬ የምችለውን ሁሉ ከማድረ ወደኋላ አልልም ሲሉም ምላሻቸውን አጠቃለዋል።