በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በታጣቂዎችና በመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል የተካሄደውን ውጊያ ተከትሎ 12 ሰዎች ታሰሩ

ኢሳት (ታህሳስ 28 ፥ 2009)

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰሞኑን በአካባቢው ተቃዋሚ ታጣቂዎችና በመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል የተካሄደውን ውጊያ ተከትሎ በአሶሳ 12 ሰዎች መታሰራቸው ተነገረ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች አቶ ሃሊድ ናስር ለኢሳት እንደገለጹት የታሰሩት ሰዎች ሰላማዊ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው።

በቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ /ቤህነን/ እና በህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት መከላከያ ሃሙስና አርብ በተካሄደ ውጊያ 8 የአገዛዙ ወታደሮች መገደላቸው ተነግሯል። ከንቅናቄው በኩልም አንድ ሰው ተገድሏል ተብሏል።

በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በተለያዩ አቅጣጫዎች የታጠቁ አማጺያን በህወሃት ኢህአዴግ የሚመራውን መንግስት እየተፋለሙ ናቸው። በሃገሪቱ ለነጻነት ከሚፋለሙ አማጺያን መካከል የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ አንዱ ነው። ይኸው ቡድን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሸርቆሌ አካባቢ በከፈተው አዲስ ጥቃት በመከላከያ ሰራዊት አባላትና በክልሉ ልዩ ሃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን እየገለጸ ይገኛል።

የድርጅቱ ሃላፊ አብድላሂ አላዲህ ሰሞኑን ለኢሳት እንዳታስወቁት ንቅናቂያቸው የመንግስት ሃይሎች ላይ ባደረሰው ጥቃት ከ51 በላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ገድሏል። በርካታ ሰላማዊ ሰዎችም በውጊያው ሳቢያ መገደላቸውን ተነግሯል። ይህንን ግጭት ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች ታስረው ወደ አሶሳ መወሰዳቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች አቶ ሃሊድ ናስር ለኢሳት ገልጸዋል።

እንደ አቶ ሃሊድ ገለጻ፣ በሸርቆሌና መንጌ አካባቢዎች ሃሙስና አርብ እየተካሄደ ባለው ውጊያ 4 ሰዎች ከመከላከያ ሲገደሉ 4ቱ ደግሞ ከልዩ ሃይል አባላት 2 ሞተዋል። አካባቢው በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መሆኑን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪው ይነገራሉ።

አቶ ሃሊድ እንዳሉድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝ እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየተባባሰ መጥቷል። እንደርሳቸው ገለጻ በክልሉ 1ሺህ በላይ እስረኞች ከህግ ውጪ ታስረው ይገኛሉ። በዚሁ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተነሳ ህዝቡ ለነጻነቱ እየታገለ መሆኑን አቶ ሃሊድ አስታውቀዋል።