ኢሳት (ታህሳስ 19 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ጀግና አትሌት ሻንበል ምሩፅ ይፍጠር ፍትሃተ ጸሎት በካናዳ ቶሮንቶ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ተከናወነ። በዚህ ሳምንት አስከሬን ወደ ትውልደ ሃገሩ ኢትዮጵያ እንደሚሄድም ለማወቅ ተችሏል። ባለፈው ሳምንት ሃሙስ ታህሳስ 13, 2009 ምሽት ካናዳ ቶሮንቶ ህይወቱ ያለፈው ታላቅ አትሌት ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር በርካታ ኢትዮጵያውያን በታደሙበት እጅግ ደማቅና ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ማክሰኞ ታህሳስ 18 2009 ጸሎተ ፍትሃቱ የተካሄደ ሲሆን፣ የኤርትራ ኦርቶዶክስ የሃይማኖር አባቶችም በፍትሃተ ጸሎቱ ተሳትፈዋል።
በተለያየ ሃይማኖር ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በስነስርዓቱ መገኘታቸውን መረዳት ተችሏል።
በካናዳ ቶሮንቶ ረጅም አመታት ያሳለፈው ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር ከኢትዮጵያውያን ጋር ሁሉ ጥሩ ግንኙነት የነበረውና ጠንካራ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እንዲኖርም ሲሰራ መቆየቱ ተመልክቷል።
በካናዳ ቶሮንቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ማሪያም ቤተክርስቲያን አስተዳደር ሊቀካህናት ምሳሌ እንግዳን ጨምሮ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ለፕሮግራሙ ሂደትና ስኬት ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ አትሌክስ ውስጥ እጅግ ደማቅ ታሪክ ከጻፉት አትሌቶች በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አንዱ የሆነው የሻምበል ምሩፅ ይፍጠር አስከሬን በዚሁ ሳምንት መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓጓዝ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የቀብሩም ስነስርዓት የሚያስተባብር ኮሚቴ በሃገር ቤት መቋምቋሙ ማወቅ ተችሏል።