ኢትዮጵያ አስደንጋጭ የዕዳ ክምችት ካለባቸው 10 ሃገራት መካከል አንዷ ናት ተባለ

ኢሳት (ታህሳስ 19 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አስደንጋጭ ነው የተባለው የውጭ ዕዳ ክምችት ካለባቸው 10 ሃገራት መካከል አንዷ ሆና ተፈረጀች።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከ 2015 አም የሃገሪቱ የዕዳ ክምችት ይፋ ያደረገ አንድ አለም አቀፍ መጽሄት የሃገሪቱ የዕዳ ክምችት 22 ቢሊዮን አካባቢ እንደነበር በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል። ይሁንና በተያዘው የፈረንጆች 2016 አም ይኸው የዕዳ ክምችት ወደ 36 ቢሊዮን ዶላር ኣካባቢ መድረሱ ሲገለጽ ቆይቷል።

ከአህጉሪቱ በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ከተዘፈቁት አስር ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በሰባተኛ ደረጃ የተቀመጠች ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካና ግብፅ እያንዳንዳቸው እንደቅደም ተከተላቸው የ143 እና የ46 ቢሊዮን ዶላር ባለዕዳ መሆናቸውን እንድ Answers Africa የተሰኘ መጽሄት አቅርቧል።

ሱዳን፣ ሞሮኮ፣ ቱኒሲያ፣ እና አንጎላ ከሶስተኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን፣ ጋና፣ ታንዛኒያ ናይጀሪያ ከ15-10 ቢሊዮን የሚደርስ ዕዳን በመያዝ እስከ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዕዳ ክምችት እንደፈረጆቹ አቆጣጠር በ2015 አም 50 በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ የሃገሪቱ አመታዊ ምርት የሚሸፍን የነበረ ሲሆን፣ ይኸው አህዝ እዳው በመጨመሩ ሳቢያ ወደ 55 በመቶ አካባቢ ማሻቀቡን ለመረዳት ተችሏል።

መንግስት እያካሄደ ያላቸው በርካታ የልማት ፕሮጄክቶች በሃገር እና በውጭ አበዳሪ አካላት የሚከናወኑ በመሆናቸው የሃገሪቱ የዕዳ ክምችት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

የመንገድ፣ የቴለኮሙኒኬሽን፣ እንዲሁም የሃይል ማመንጫ ግንባታዎች አብዛኞቹ ከብድር በሚገኝ ገንዘብ እየተከናወኑ ያሉ በመሆናቸው ድርጊቱ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የራሱን ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ የፋይናንስ ተቋማት ይገልጻሉ።

ይሁንና የመንግስት ባለስልጣናት ሃገሪቱ እየተበደረች ያለው ገንዘብ እዳ የመክፈል አቋሟን ያገናዘበ በመሆኑ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ተፅዕኖ አያመጣም በማለት እየቀረቡ ያሉ ማሳሰቢያዎችን ያስተባብላሉ።

ሃገሪቱ ከተለያዩ አለም አቀፍ አበዳሪ አካላት እየወሰደች ያለው ብድር ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልበት በመሆኑ ዕዳው ለረጅም አመታት በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ እንቅፋት እንደሚሆን የምጣኔ ባለሙያዎች አስረድተዋል።

በተያዘው 2009 አም መንግስት ለሃገሪቱ ከተበጀተው ወደ 13 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ውስጥ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ለውጭ ዕዳ ክፍያ እንዲውል ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።

ይሁንና ሃገሪቱ እየወሰደች ያለው እዳና እየከፈለች ያለው ገንዘብ የሚመጣጠን ባለመሆኑ የእዳ ክምችቱን ክፍሎ ለማጠቃለል ረጅም ጊዜን ይወስዳል ተብሎ ይገመታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ወጭ ንግድ እየቀነሰ መምጣቱ በውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ተፅዕኖን በማሳደር የሃገሪቱን የእዳ ክፍያ አቅም እየተፈታተነው እንደሚገኝም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የአለም ባንክ በበኩሉ ሃገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ዕዳ ክፍያ ለማሻሻል የፖሊስ ማሻሻያ በአስቸኳይ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ውጭ ንግድ ገቢ እና የውጭ ምንዛሪ ክምችት እየቀነሰ መምጣት የሃገሪቱ የዋጋ ግሽበት እንዲያድግ ምክንያት መሆኑም ተመልክቷል።

ያለፈው ወር አጠቃላይ የሃገሪቱ የዋጋ ግሽበትን ይፋ ያደረገው የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የዋጋ ግሽበቱ ከ5.6 በመቶ ወደ ሰባት በመቶ ማደጉን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የምግብ ዋጋ ንረት ለዋጋ ግሽበቱ መጨመር ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ኤጀንሲው በሪፖርቱ አመልክቷል።