ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዝዋይ እስር ቤት ውስጥ በጽኑ ታሞ ባቱ ሆስፒታል ገባ

ታኅሣሥ ፲፰ (አሥራ ስምንት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የሶስት ዓመት እስራት ተፈርዶበት በዝዋይ እስር ቤት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታህሳስ18 ቀን 2009 ዓ.ም በፀና ታሞ በአንፑላንስ ተጭኖ ዝዋይ በሚገኘው ባቱ አጠቃላይ ሆስፒታል መግባቱ ታውቋል።

በተደጋጋሚ ጊዜያት ከቤተሰቦቹ እና ሕጋዊ ጠበቃው ጋር እንዳይገናኝ ሲደረግ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ የእስር ቤቱ ወታደሮች ወደ ሆስፒታል ይዘውት በሚገቡበት ወቅት በአቅራቢያው የሚገኙትን ሰዎች እንዲርቁ አድርገዋል። በዚህም ምክንያት የተመስገን የሕመም ደረጃ ምን ያህል እና በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ እንዳልተቻለ ቤተሰቦቹ ስጋታቸውን ገልፀዋል። ይህን ዜና እስካጠናከርንበት እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቃሬዛ ተጭኖ ከገባበት ዝዋይ ባቱ ሆስፒታል ያልወጣ ሲሆን የሕመሙን ዓይነት ቤተሰቡ እንዲያውቁት አልተደረገም።

”የዛሬው የፈረቃ መሪ ሻለቃ ንጉሴ ጨምሮ ዝዋይ እስር ቤት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም እስከ ዛሬ በተመሰገን ላይ ለደረሰው እና ለሚደርሰው ነገር ሁሉ መንግስት ሙሉ ሃላፊነቱን ይወስዳል” ሲል የጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ ወንድም የሆነው ታሪኩ ደሳለኝ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስነብቧል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከወራት በፊት የአመክሮ ጊዜውን ጨርሶ መፈታት ይገባው የነበረ ቢሆንም የእሱ መጽሐፍ እና ጹሁፎች አሁን ለተፈጠረው ሕዝባዊ እንቢተኝነት መቀስቀስ መንስዔዎች ናቸው በሚል ምክንያት ከሕግ አግባብ ውጪ በሕመም ላይ እያለ በኮማንድ ፖስቱ በእስር እንዲማቅቅ መደረጉ ይታወሳል።