ታኅሣሥ ፮ (ስድስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል በተለያዩ የክልል ቢሮዎችና የዞን መምሪያዎች በግንባታ ስራ ላይ ተቀጥረው የሚገኙ መሃንዲሶች ስራቸውን በመልቀቅ ላይ ያሉት በቅርቡ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ወጣቶች የስራ ዕድል አማራጮችን ለማስፋፋትና ለማበረታታት በሚል የተዘጋጀውን መመሪያ ቁጥር 27/2009 ተንተርሶ ነው፡፡
መመሪያው ከተለያዩ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው ስራ የሌላቸውን ወጣቶች ወደ ስራ ለማስገባትና የስራ ዕድል አማራጮችን ለመፍጠር የሚል ቢሆንም፤ ወጣቶችን ለማበረታታት በተዘጋጀው መመሪያ ግን በርካታ የምህንድስና ባለሙያዎች ስራቸውን በመልቀቅና ከባለስልጣናቱ ቤተሰቦች ጋር በማህበር በመደራጀት በርካታ ግንባታዎችን ያለ ውድድር በመረከብ ላይ መሆናቸውን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
ይህ መመሪያ ገዥው ፓርቲ እየደረሰበት ያለውን ጠንካራ ተቃውሞ ለማብረድ በማሰብ ያለምንም ቅድመ ዝግጅት እና የዘርፉን ባለሙያዎች ባላሳተፈበት መልኩ በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ የተዘጋጀ በመሆኑ ለችግሩ መፈጠር ዋና ምክንያት ሆኗል።
በመላ አማራ የሚገኙ ከደረጃ ሰባት ጀምሮ እስከ ደረጃ አስር ድረስ ያሉ የስራ ተቋራጮች ከአሁን በፊት ሲሳተፉበት የነበረውን እስከ ብር አምስት ሚሊዮን አራት መቶ ሽህ ብር የሚደርስ የህንጻ ግንባታ፣እስከ ሰባት ሚሊዮን አምስት መቶ ሽህ ብር የሚደርስ የመንገድ ስራ፣ለጠቅላላ ስራ ተቋራጭ አስከ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር እና ለመጠጥ ውሃና ለመስኖ ስራ የሚመደቡት እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ስራዎች ሙሉ በሙሉ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሰጥ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ይህ ውሳኔ ከአሁን በፊት በዚህ ስራ ላይ ተሰማርተው ይተዳደሩ የነበሩትን በሽዎች የሚቆጠሩ የዘርፉ ባለሙያዎችንና በስራቸው ይተዳደሩ የነበሩትን በርካታ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ ዕድል ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ዘግቷል፡፡ መመሪያው በስራው ላይ ተሰማርተው ለነበሩት አካላት ያስቀመጠው የስራ ሃሳብ ወይም አቅጣጫ ባለመኖሩና በዝምታ በመታለፉ፣ የመንግስትን ሃሳብ ለማዎቅ መቸገራቸውን የሚናገሩት የግንባታ ስራ ተቋራጮችና በስራቸው የሚተዳደሩ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ፣ ቅሬታቸውን ለክልሉ መንግስት በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
መመሪያው አዲስን ስራ የፈጠረ ሳይሆን ቀድሞ ይሰሩ የነበሩትን ባለሙያዎች ስራ ቀምቶ በመውሰድ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያደረገ ከመሆኑ ባሻገር በአሁኑ ሰዓት በዕድሉ በመጠቀም ላይ ያሉት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለስልጣናት ያደራጇቸው ቤተሰቦቻቸውና ስራቸውን እየለቀቁ መሃንዲሶች በመደራጀት ከፍተኛ ትርፍ ያለምንም ውድድር እየሰበሰቡ ሌለውን ዜጋ የበይ ተመልካች እንዳደረጉት ባለሙያዎች በቅሬታ ይናገራሉ፡፡
ምንም ልምድ የሌላቸውን ወጣቶችን በግንባታው ስራ በማሰማራት በስራው ላይ ጉድለት ከማሳደርና ወጣቶችን የሌሎች መጠቀሚያ ከማድረግ በመቆጠብ በስራው ላይ ከፍተኛ ልምድ ካላቸው የግንባታ ባለሙያዎች ጋር በማቀናጀት ስራውን በአግባቡ የሚሰሩበትን አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ባለሙያዎች ተናግረዋል።
በክልሉ በተካሄዱ በርካታ ግንባታዎች ላይ ለብዙ አመታት በግንበኝነት ፣በአናጺነት፣በለሳኝነትና በመሳሰሉት የግንባታ ስራ ዘርፎች ላይ ያሉና በስራቸው በርካታ ስራ አጥ ወጣቶችን በመያዝ ቤተሰብ የመሰረቱ፣ የመንግስትን መመሪያ በመከተል ንግድ ፈቃድ አውጥተው ሲሰሩ የነበሩ ዜጎች እጣፋንታ በመመሪያው ላይ ባለመከታቱ በአስቸኳይ እንዲሻሻልላቸው ጠይቀዋል።