ኢሳት (ታህሳስ 5 ፥ 2009)
ሳውዲ አረቢያ በየመን እየወሰደች ያለው ወታደራዊ ዕርምጃ ያስነሳውን ቅሬታ ተከትሎ አሜሪካ ለአገሪቱ የምታደርገውን የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ ለመቀነስ ወሰነች።
ካለፈው አመት ጀምሮ ሳውዲ አረቢያ ካለፈው አመት ጀምሮ ሳውዲ አረቢያ በየመን አማጺያን ላይ እየፈጸመች ያለው የአየር ጥቃት ለበርካታ ንጹሃን ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የመናዊያን ሲገልፁ ቆይተዋል።
በተለይ በጥቅምት ወር በአንድ የቀብር ስነስርዓት ላይ በተፈጸመ የሳውዲ አረቢያ የአየር ጥቃት 140 ሰዎች መሞታቸው በተለያዩ ሃገራት ዘንድ ቁጣን ቀስቅሶ ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ ለሳውዲ አረቢያ በምታቀርበው የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ ላይ የማስተካከያ ዕርምጃን ለመውሰድ የወሰነች ሲሆን፣ ኢላማዎችን ለይቶ ለመምታት የሚውሉ መሳሪያዎች ለሳውዲ አረቢያ እንዳይሸጡ መደረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።
አሜሪካ ለሃገሪቱ የምታቀርበው የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዲቀንስ ብታደርግም የስልጠናና የስለላ መረጃ ልውውጦች ቀጣይ እንደሚሆኑ ገልጻለች።
በየመን የአየር ጥቃት በመፈጸም ላይ ያሉ የሳውዲ አረቢያ ፓይለቶች ልዩ ስልጠናን እንዲያገኙ እንደሚደረግም የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ኔድ ፕራይስ ለመገኛኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ሳውዲ አረቢያ በየመን እየወሰደች ባለው የአየር ጥቃት ትምህርት ቤቶች የህክምና እንዲሁም የሲቪል አገልግሎት መስጫ ተቋማት መውደማቸው ይነገራል።
በየመን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውንና ከሶስት ሚሊዮን በላይ የመናዊያን ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ሳውዲ አረቢያ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ያላቸውን የፕሬዚደንት አብድራቡ ማንሱርን መንግስትን በመደገፍ በሃቲ አማጺያን ላይ ወታደራዊ ዕርምጃን በመውሰድ ላይ ስትሆን ኢራን ደግሞ ለሃቲ ቡድን ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች።
የአልቃይዳ እንዲሁም የአሲስ ታጣቂ ሃይሎች በየመን በስፋት የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ሃገሪቱ ወደማያባራ የርስ በርስ ጦርነት ትገባለች ተብሎ ተሰግቷል።
አሜሪካ ለሳውዲ አረቢያ በምታቀርበው የጦር መሳሪያ አቅርቦት ላይ የማስተካከያ ዕርምጃን ብትወስድም በሁለቱ ሃገራት መካከል በቅርቡ የተፈረመ የሶስት ቢሊዮን የዘመናዊ የጦር ሄሊኮፕተሮች ስምምነት ግን እንደማይቋረጥ ወታደራዊ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ሳውዲ አረቢያ በበኩላ በንጹሃን ሰዎች ላይ አድርሰዋለች የተባለውን ቅሬታ በማስተባበል ጉዳት እንዳይደርስ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗን ትገልጻለች።