ኢሳት (ኅዳር 9 ፥ 2009)
በቅርቡ ከሶማሊያ ቁልፍ ከተባሉ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው የወጡ የኢትዮጽያ ወታደሮች ቁጥር ወደ 12ሺ አካባቢ እንደሚደርስ አፍሪካ ኮንፊደሻል የተሰኘና በወታደራዊ ደህንነት ዙሪያ ዘገባን የሚያቀርብ መጽሄት ዘገበ።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ባኮ፣ ሂራን እና ጋልጋዱድ ከሚባሉ የማዕከላዊና ደቡባዊ የሶማሊያ ግዛቶች ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ዘገባን ያቀረበው መጽሄቱ ከሶስቱ ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎችና የማዘዣ ጣቢያዎች ለቀው የወጡት የኢትዮጵያ ወታደሮች ቁጥር ወደ 12ሺ እንደሚገመት አመልክቷል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር ካሰማራችው ወደ 4ሺ 500 ወታደሮች በተጨማሪ ቁጥሩ የማይታወቅ ወታደርን በተለያዩ የሶማሊያ ግዛቶች ስታሰፍር መቆየቷ ይነገራል።
በኢትዮጵያ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከልቶ ወታደሮቹ ለአመታት ይዘው የቆዩትን ስፍራ ለቀው የወጡ ሲሆን፣ የተለያዩ አካላት ዕርምጃውን ወታደሮቹ በሃገር ውስጥ ለማሰማራት ታስቦ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ይሁንና መንግስት የወታደሮቹ ከይዞታቸው መልቀቅ ከአዋጁ ጋር ግንኙነት እንደሌለው በማስተባበል የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለሶማሊያ መንግስት ድጋፍ ባለማድረጉ ምክንያት በሃገሪቱ የጸጥታ ክፍተት መፍጠሩን ገልጿል።
አፍሪካ ኮንፊዴንሻል መጽሄት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ወደ 12ሺ የሚደርሱ ወታድሮቿን ብታስወጣም አሁንም ከኦጋዴን ሶማሊ የጸጥታ አባላት በአካባቢው እንደሚገኙ በዘገባው አስፍሯል።
ኢትዮጵያ ምን ያህል የተናጠል ወታደሮችን በሶማሊያ አሰማርታ እንደምትገኝ ከመግለጽ ተቆጥባ የምትገኝ ሲሆን ወታደሮቹ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከታህሳስ ወር 2006 ዓም ጀምሮ መሰማራታቸው የሚታወስ ነው።