የፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ በጎንደር እንዳይካሄድ መከልከሉ ተገለጸ

ኢሳት (ህዳር 9 ፥ 2009)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረው የፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ ቢቀጥልም፣ ጎንደር ላይ ጨዋታ እንዳይካሄድ ኮማንድ ፖስቱ መከልከሉን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ። በዚህም መሰረተ የፊታችን ዕሁድ በጎንደር ሊካሄድ የታቀደ የእግር ኳስ ውድድር ተሰርዟል።

የፊታችን ዕሁድ በፋሲል ከነማና በወላዩታ ደቻ መካከል በጎንደር ስታዲየም ሊካሄድ መርሃ ግብር የተያዘለት የእግር ኳስ ውድድር ኮማንድ ፖስቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት መሰረዙ ታውቋል። ጨዋታው ከጎንደር ውጭ እንዲካሄድም መመሪያ ወርዷል።

ጨዋታው የትና መቼ እንደሚካሄድ ግን ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የሚታወቅ ነገር የለም።

ሃምሌ 5 ፥ 2008 ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በፈጠሩት ዕምቢተኝነት በአማራ ክልል የተቀጣጠለው ህዝባዊ ዕንቅስቃሴ በተለይ በጎንደር ወታደራዊ ግጭትን እያስተናገደ መምጣቱ ስልጣን ያለው ቡድን በአካባቢው ችግር እንደገጠመው በየዕለቱ የሚወጡ ዜናዎች ያስረዳሉ።

በአርሶ አደርና በነጻነት ሃይሎች እየተካሄደ ያለው ግጭት አሁን ወደ ውጊያ ደረጃ እያደገ መምጣቱም እየተሰማ ሲሆን፣ በሳምንቱ መጨረሻ የአርበኛው ግንቦት 7 ታጣቂዎች ከመንግስት ሃይሎች ጋር መዋጋታቸውን የአካባቢው ምንጮች ያሰረዳሉ። ቀሳውስትን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮች አርበኞች ግንቦት 7ትን በይፋ መቀላቀል ላይ መሆናቸውንም ንቅናቄው አውስቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳም በአዲስ አበባ ከተማ በየአመቱ የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ ለፊታችን ዕሁድ መርሃግብር እንደተያዝለለት ታውቋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ አዘጋጆች ጽ/ቤት እንዳስታወቀው 42ሺ ሰው ይሳተፍበታል ተብሎ የተገመተው ውድድር በመጪው ዕሁድ ህዳር 1 ፥ 2009 በአዲስ አበባ ጎዳና ይካሄዳል።

ይህ ውድድር ቀደም ባሉት አመታት ህዝባዊ ተቃውሞ የሚሰማበት በመሆኑ የሩጫው መስመር በቤተመንግስት በኩል እንዳይሆን መከልከሉ ይታወሳል።