የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ተገለጸ

ኢሳት (ጥቅምት 22 ፥ 2009)

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቅሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቆም በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ መንግስታዊ ባልሆኑ መስሪያ ቤቶች በሚሰሩ የዕርዳታ ሰራተኞች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረሰ እንደሚገኝ ተገለጸ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሰራተኞቹ የወደፊት ስራ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አለመታወቁም ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ እነዚህ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለውን ወከባና አፈና በመፍራት ለጋዜጠኞች ቃለምልልስ ጭምር ለመስጠት ፍርሃት እንዳለባቸው ዲቬክስ (DEVEX) በሚሰኝ የአለም አቀፍ እድገትና ብልፅግና ላይ የሚሰራ ድርጅት በድረገጹ ላይ ባወጣው ሃተታ አብራርቷል። የውጭ ሃገር የእርዳታ ሰራተኞች ቃለ-ምልልስ የማይሰጡበት ምክንያት የሰራተኞቻቸውን ደህንነት ለመጠበቅ እንደሆነም ይኸው ሪፖርት ያትታል።

የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ የአለም አቀፍ ድርጅቶች ሃላፊዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ያለውን የሰብዓዊ መብት አፈና በግልጽ ለመናገር አለመድፈራቸውን የጠቀሰው ይህ ዘገባ፣ እየተካሄደ ያለውን አፈና ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ቢግልጹ የኢትዮጵያ መንግስት የእርዳታ  አሰጣቱን ሂደት ሊያስተጓጉል ይችላል ብለው እንደሚያስቡ ዘርዝሯል። ከዚህ በተጨማሪ እነዚሁ አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ከኢትዮጵያ ልንባረር እንችላለን በሚል ፍርሃት እንዳለባቸው ሪፖርቱ ያትታል።  መንግስት የእርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ እንዳይቀሳቀ ከከለከለ እርዳታ የሚሻ ከ9 ሚሊዮን 700 ሺ የሚበልጥ ህዝብ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲል ጽሁፉ ይዘረዝራል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በኢትዮጵያ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚሰሩ የተወሰኑ የልማት ፕሮጄክቶች መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ እየወሰደ ባለው ዕርምጃ ምክንያት እየተጓተቱ እንደሆነ የድርጅቶቹን ሃላፊዎችን ዋቢ በማድረግ ድረ-ገጹ ዘግቧል።