ኢሳት (ጥቅምት 27 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት አመታዊ ጉባዔ ላይ ስጋት ማሳደሩ ተነገረ።
የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የውጭ ሃገራት ተወካዮች ከመዲናይቱ 40 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው መሄድ ከፈለጉ መንግስት ማሳወቅ እንዳለባቸው መደንገጉ ይታወሳል።
ይሁንና ለስድስት ወር ይቆያል የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ ዋጅ በቅርቡ በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሎ የሚበጠቀው የአፍሪካ ህበረት ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ስጋት ማሳደሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።
የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ምክክርን በማካሄድ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ለአፍሪካ ህብረት ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ የሃገራት መሪዎችና ልዑካን እንዲሁም ጋዜጠኞች ከመዲናይቱ ውጭ ለተለያዩ ጉዳዮች ጉብኝት እንደሚያደርጉ ምንጮች አስረድተዋል።
ይሁንና በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ ዋጅ ወደ ኢትዮጵያ ለጉባዔው መጓዝ በሚፈልጉ ልዑካን ላይ ስጋት ማሳደሩ ተገልጿል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲሰርዙ ማስጠንቀቁ ይታወሳል።
ሃገሪቱ ያወጣቸው ይኸው እገዳ በተለያዩ አካላት ዘንድ ስጋትን ማሳደሩን የገለጹት ምንጮች ማሳሰቢያው ቀጥተኛ ያልሆነ ፖለቲካዊ መልዕክት ማስተላለፉን አስረድተዋል።
የአሜሪካ መንግስት ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ያወጣውን ማሳሰቢያ ተከትሎ ኢትዮጵያ ተቃውሞን አቅርባለች።
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ያወጣው የጉዞ ክልከላ የኢትዮጵያ ሁኔታ የማይገልጽ እንደሆነ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የአዋጁ መውጣት ተከትሎ ወደ ሃገሪቱ የሚጓዙ የቱሪስቶች ቁጥር መቀነሱ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ያካሄደዋል ተብሎ የሚጠበቀው ልዩ የመሪዎች ጉባዔ አስቸኳይ አዋጅን ተግባራዊ ባደረገች አባል ሃገር ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል ተብሎ ተጠብቋል።
በአዲስ አበባ የሚካሄደው 28ኛው የህብረቱ ጉባዔ የህብረቱ አዲስ ሊቀመንበር ከመምረጥ በተጨማሪ በአፍሪካ ባሉ የጸጥታ ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራል ተብሎ አጀንዳ ተቀምጧል።