ህዳር 14 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ዛሬ ህዳር 14 ቀን 2004 ዓም ከቀኑ በ9 ሰአት በዋለው ችሎት ላይ ሁሉም እስረኞች እጆቻቸው በካቴና ታስሮ በፍርድ ቤቱ ተገኝተዋል።
የፍርድ ቤቱን ሄደት ለመከታተል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢገኙም፣ ፖሊሶች ግን 20 ሰዎችን ብቻ እንደሚያስገቡ በመግለጣቸው አብዛኛው ህዝብ ሁኔታውን በውጭ ሆኖ ለመከታተል ተገዶአል።
ፍርድ ቤቱ ከአንደኛውና ከአራተኛው ክሶች በስተቀር ሌሎች ክሶች መሰረተ ቢስ ናቸው፣ አንደኛውና አራተኛውም ክሶች ቢሆኑ መሻሻል የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ አቃቢ ህግ ክሱን አሻሽሎ ለህዳር 20 ቀን ይዞ እንዲቀርብ በማለት ወስኖአል።
ከተለያዩ ኢምባሲዎች የመጡ ዲፕሎማቶችና የውጭ ጋዜጠኞች በብዛት መገኘታቸውን ዘጋቢያችን ገልጦአል።
በተራ ቁጥር አንድ እና አራት ላይ የሰፈሩት ወንጀሎች ሽብር ለመፈጸም ማቀድና ከኤርትራ መንግስት ጋር አብሮ መስራት የሚሉት ናቸው።
አቶ መለስ ዜናዊ አስተማማኝ የሆኑ መረጃዎችን በእጃችን ሳንይዝ አንድም ሰው አላሰርንም በማለት በቅርቡ በፓርላማ ላይ ቢናገሩም፣ እስካሁን በታዬው ሄደት ግን የሚጨበጥ ማስረጃ እንደሌላቸውና ከፍተኛ ትዝብት ውስጥ እንደጣላቸው እየታዬ ነው።
እነ አርቲስ ደበበ እሼቱ ” መንግስት ጠርጥሮ አሰረ፣ መንግስት ፈታ” በሚል ተራ ምክንያት መለቀቃቸው ይታወቃል።