ህዳር 12 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ጉሬል በተባለችዉ ከኢትዮጵያ ድንበር በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለች ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች እንደገለፁት ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችና ታንኮች የያዙ የኢትዮጵያ ወታደሮች እሁድ እለት ድንበር አቋርጠዉ ሶማሊያ መግባታቸዉን ተናግረዋል።
የሶማሊያ መንግሰት ቃል አቀባይ አብዱራህማን ኡመር ኦስማን የኢትዮጵያ ወታደሮች በአለም አቀፍ ዉክልና ወይንም ከመንግስታቸዉ ጋር በሚደረግ ስምምነት ካልሆነ በስተቀር መግባት እንደማይችሉና በዚህ ረገድ በቅርብ የተፈፀመ ስምምነት ያለመኖሩን ገልፀዋል።
በሶማሊያ ጋልጉዱድ ክልል በምትገኘው ጉሬል ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች መታየታቸው የአይን ምስክሮች ቢገልፁም የኢትዮጵያ መንግስት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ “በአሁኑ ሰዓት ምንም ዓይነት የኢትዮጵያ ጦር በሥፍራው የለም ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ ዘልቆ መግባቱ 3ኛ የዉጊያ ግንባር ወይንም ቀጣና እንደሚከፍት ይገመታል። በደቡብ ኬንያ አዋሳኝ አካባቢ በኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ የተባለው የ “አል ሻባብ” ታጣቂዎችን ለመምታት ኬንያ ጥቃት መጀመሯ የሚታወስ ሲሆን በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ደግሞ 9000 አባላት ያሉት የአፍሪቃ ህብረት ጦር መስፈሩ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካ ሰው አልባ የጦር ጀት ከአርባ ምንጭ እየተነሳ የስለላ ስራ እንዲያካሄድ መፍቀዱን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸዉ ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቤሌዲ-ወይን እና ቺል-በር በተባሉ፣ በአማፅያን ቁጥጥር ስር በነበሩ አካባቢዎች ዉስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች በመግባት ላይ እንደሚገኙ በመስማታቸው ፣ የአልሸባብ ወታደሮች የሚቆጣጠሯቸዉን ኬላዎች በመልቀቅ በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ተጭነዉ ወዳልታወቀ ስፍራ መጓዛቸዉን ተናግረዋል።
እንደ መረጃ ምንጮቹ ገለፃ የአልሸባብ ወታደሮች የኬንያ ወታደሮች ሲገቡ እንዳደረጉት ሁሉ ለጥቂት ጊዜ ወታደራዊ ትጥቆቻቸዉን እያወለቁ በሰላማዊዉ ህዝብ መሃል ተደባልቀዉ ሊቆዩ እንደሚችሉና ሁኔታዉን ተመልክተዉ እንደሚሰባሰቡ አልሸሸጉም።
የኢትዮጵያ ጦር በ2006 ሶማሊያ ከገባ በሁዋላ በአካባቢዉ ሰላም ሳያሰፍን ይልቁንም አልሸባብን ፈጥሮ በ2009 መዉጣቱ ይታወቃል።