የንግድ ሚኒስቴር 16 ታዋቂ የቡና ላኪ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ምርት ገባያ ውስጥ እንዳይሳተፉ አዘዘ

ህዳር 12 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-እገዳው ከተጣለባቸው  ኩባንያዎችና ግለሰቦች መካከል ካፍ ኢንተርናሽናል፣ አብዱልቃድር ሙሀመድ አሊና አብዱል አሊ የተባሉት ይገኙበታል።

ንግድ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ በላከው ደብዳቤ ነጋዴዎቹ የታገዱት በመጋዘን ያስቀመጡትን ክምችት ባለማሳወቃቸው ነው ብሎአል። ይህ የቅርብ እገዳ በአጠቃላይ በአለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ የታገዱትን የቡና ላኪዎች ቁጥር 57 አድርሶታል።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ነጋዴ ለአዲስ አበባው የኢሳት ወኪል እንደተናገሩት እርምጃው የቡና መላክን ስራ ሙሉ በሙሉ ጉና ንግድ የተባለው የህወሀት ኩባንያ በብቸኝነት እንዲይዘው ለማድረግ ታስቦ የተወሰደ ነው።

ጉና ንግድ ወደ ቡና መላክ ስራ በቅርቡ መግባቱን ያወሱት ባለሀብቱ፣ ይሁን እንጅ ከመንግስት በሚደረግለት ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዋነኛው የቡና ላኪ ድርጅት እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

“ዋና ዋናዎቹ የቡና ላኪዎች ቡና ከመግዛት እንዲታገዱ ከተደረገ በገበያው ውስጥ ብቸኛው ገዢኛ ሻጭ ጉና የንግድ ድርጅት ይሆንና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነው የቡና ገበያ በህወሀት እጅ ይወድቃል ሲሉም ፍርሀታቸውን” ገልጠዋል።

“ህወሀት እስካሁን ሊቆጣጠረው ያልቻለው የቡና ገበያውን ነበር፣ አሁን ግን ይህንንም ለመቆጣጠር የሚችልበትን መንገድ ዘርግቷል፣ ከዚህ በሁዋላ ህወሀት የማይቆጣጠረው  የንግድ ተቋም አይኖርም፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሀይል ሁሉ በአንድ ፓርቲ ስር ተጠቃሎ እየገባ ነው” ባለሀብቱ በምሬት ተናግረዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ድርጅታቸው ከቡና የንግድ ስራ እንዲወጣ በመደረጉ ከባንክ የተበደሩትን ገንዘብ በወቅቱ ለመክፈል አልቻሉም። ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሬ የምታገኘው ከቡና መሆኑ ይታወቃል። ባለፈው አመት አገሪቱ ከቡና ከ900 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ አግኝታለች።