ኢሳት (መስከረም 10 ፥ 2009)
አትሌት ፈይሳ ለሊሳና ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የኢሳት የአመቱ ምርጥ ሰው በሚል ተመረጡ። የ2008 የአመቱ ምርጥ ሰው በሚል በአንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ስም የተሰየመውን ሽልማትም በተወካዮቻቸው አማካኝነት ተቀብለዋል።
የኢሳት የአዲስ አመት ዝግጅት ባለፈው ዕሁድ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በተካሄደበት የሽልማት ስነስርዓት የሃይማኖት አባቶች መንፈሳዊና ሃገራዊ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሃጂ ነጂብ መሀመድና ከወንጌላውያን ፓስተር ያሬድ ጥላሁን በተገኙበት በዚህ ዝግጅት ለኢሳት ስቱዲዮ ስራ የሚያገለግሉ ኮምፒውተሮችን ለመግዛት ከ30 ሺህ ዶላር የሚበልጥ ድጋፍ ተበርክቷል።
ኢሳት በየአመቱ በኢትዮጵያ አሮጌ አመት ፍጻሜ የሚያካሄደውን የዓመቱ ምርጥ ሰው ምርጫ በኢሳት አድማጮችና ተመልካቾች ድምፅ መሰረት ሲያካሄድ መቆየቱ ይታወሳል። በዚህም አመት በተካሄደው የህዝብ ተሳትፎ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱና አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ተቀራራቢ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘታቸው እንዲሁም ጥቂት የማይባሉ መራጮች ለሁለቱም በአንድነት ድምፅ በመስጠታቸው የምርጫውን ሂደት የሚከታተለው የኢሳት ኮሚቴ፣ ሁለቱንም የአመቱ ምርጥ ሰው በማለት መሰየሙ በዝግጁት ላይ ተብራርቷል።
ሁለቱ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ በማንቀሳቀስና፣ አለም አቀፋፊ ትኩረት እንዲያገኝ በማድረግ አስተዋጾአቸው የጎላ መሆኑንም ተመልክቷል።
የኢሳት የአመቱ ምርጥ ሰው ሽልማትን በ2006 አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ እንዲሁም በ2007 ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ማግኘታቸው ሲታወስ፣ የመጀመሪያውን የኢሳትን የአመቱ ምርጥ ሰው ሽልማት ያገኘው ጋዜጠኛና አክቲቪስት አበበ ገላው መሆኑ ማስታወስ ተችሏል።
ጋዜጠኛ አበበ ገላው፣ ግንቦት 10/2004 በዋሽንግተን ሬገን ህንጻ በአቶ መለስ ዜናዊ ላይ ተቃውሞ በቀረበበት አመት መመረጡም ታውቋል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን መታገታቸውን ተከትሎ ሲመረጡ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የዩኒቨርስቲ መምህርነታቸውን ጥለው ለትግል ወደ ኤርትራ መሄዳቸውን ተከትሎ መመረጣቸውም ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በዚህ የኢሳት የአዲስ አመት ዝግጅት ላይ የተካሄዱ የሃይማኖት አባቶች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት ከመግደል እንዲታቀብና ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።