በጎንደርና ባህርዳር ከተሞች ለ6 ቀናት የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ ተጀመረ

ኢሳት (መስከረም 9 ፥ 2009)

የጎንደርና ባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ለሶስተኛ ጊዜ ለስድስት ቀን የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ ሰኞ ጀመሩ።

የስራ ማቆም አድማ መጀመሩን ተከትሎ በሁለቱ ከተሞች የሚገኙ አብዛኛቹ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራ ማቆማቸውንና አድማው ነዋሪው ያለውን ተቃውሞ በተከታታይ ለማሳየት ያለመ መሆኑን ነዋሪዎች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

በባህርዳር ከተማ ሰፍረው የሚገኙ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቀበሌ 11 እና 13 አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሃይል እንዲከፍቱ ሙከራን ቢያደርጉም የንግድ ባለቤቶች ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን እማኞች ገልጸዋል።

በከተማዋ ስብሰባን እያካሄዱ የሚገኙ የብሄረ-አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብዓዴን) አመራሮች ሰኞ ከሰዓት በኋላ የከተማ ሽማግሌዎች በጉዳዩ ዙሪያ እንዲመክሩ ለማድረግ ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታም በጎንደር ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ሰኞ የጀመሩትን የስድስት ቀን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ከተማዋ ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆና መዋሏን ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የከተሞቹ ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱና መንግስት የሚፈፅመውን ግድያ በአስቸኳይ እንዲያቆም በመጠየቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በሃምሌ ወር በጎንደርና በባህርዳር ከተሞች የተጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከ50 የሚበልጡ ነዋሪዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ቁጥራቸው በአግባቡ ያልታወቀ ነዋሪዎችም ለእስር መዳረጋቸው እማኞች ሲገልፁ ቆይተዋል።

ሰኞ ለሶስተኛ ቀን የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ከመጠየቁ በተጨማሪ ነዋሪዎች አሁንም ድረስ በመንግስት ላይ ያለውን ተቃውሞ ለማሳየት ያለመ መሆኑን ከኢሳት ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ ነዋሪዎች አስረድተዋል።