መስከረም ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል በህወሃት አገዛዝ ላይ የሚካሄደው የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል ዛሬም እንደወትሮው በስራ ማቆም አድማ ቀጥሎ ውሎአል።
ሁለቱ ታሪካዊ ከተሞች በአንድ ቀን የጀመሩት የስራ ማቆም አድማ፣ የክልሉ ህዝብ ከእንግዲህ የህወሃትን አገዛዝ ተመልሶ ማየት እንደማይፈልግ ማሳያ ነው ይላሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ወገኖች።
አብዛኛው ህዝብ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ የሚተዳደር ቢሆንም፣ የጎንደር እና ባህርዳር ህዝብ ችግሮቹን ሁሉ ችሎ የሚያደርገው የስራ ማቆም አድማ ታሪካዊ ሲሆን፣ አድማው በመንግስት የሚተዳዳሩትን ሰራተኞች ሳይቀር ማጠቃለሉ ልዩ ያደርገዋል። በተለይ ነጋዴውና ማህበረሰብ እና ወጣቱ ትግሉን በግንባር ቀደምነት እየመራ መሆኑ፣ ለወጣቱ ቆሜያለሁ እንዲሁም ነጋዴውን በልማት አበልጽጌዋለሁ ለሚለው ገዢው ፓርቲ ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ኪሳራ አምጥቶበታል።
በክልሉ በ2008 ዓም መጨረሻ ላይ ተካሂዶ በነበረው ከፍተኛ ህዝባዊ እምቢተኝነት የአደባባይ ተቃውሞ ገዢው ፓርቲ አጋዚ የተባሉ ወታደሮችን አሰልፎ፣ በርካታ ወጣቶችን ገድሏል። ብዙዎችን ወደ ብርሸለቆ እስር ቤት በመውሰድ እያሰቃያቸው ነው። የህዝቡን ጥያቄ ከግምት ባለማስገባት ወይም የክልሉን ህዝብ በናቀ ስሜት ለጥያቄያቸው መልስ ከመስጠት፣ የንግድ ድርጅቶችን ማሸግ፣ ወጣቶችን እያደኑ ማሰር ከዚያም አልፎ መሳሪያ ወደ መቀማት ተሸጋግሯል። እነዚህ ድርጊቶች የክልሉን ህዝብ በእጅጉ ከማበሳጨታቸውም በተጨማሪ፣ ከህወሃት አገዛዝ ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር አይቻልም ብሎ አቋም ይዞ ትግሉን እስከመጨረሻው እንዲገፋበት እያደረገው መሆኑን ታዛቢዎች ይገልጻሉ።
ዛሬ በተደረገው ህዝባዊ የስራ ማቆም አድማ ሱቆቻቸውን እና የንግድ ድርጅቶቻቸውን የዘጉ ሰዎችን ቤታቸው ድረስ በመሄድ ማሰር መጀመሩ አገዛዙ ምን ያክል ተስፋ እየቆረጠ እንደመጣ የሚያሳይ ነው በማለት አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። የንግዱ ማህበረሰብ በጠቅላላ በአንድነት ማደሙ ገዢው ፓርቲ ክፍተት አግኝቶ የመከፋፈል ስራ እንዳይሰራ አድርጎታል። ይህንኑ የሚቆጣጠሩ ወጣቶች ራሳቸውን አደራጅተው ማንኛውም የአገዛዙን ሴራ ለማክሸፍ መቻላቸው በባህርዳርና ጎንደር የገዢውን ሃይል ሊገዳደር የሚችሉ ጠንካራ ወጣት አመራሮች እየወጡ መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉ ያነጋገርናቸው ሰዎች ይናገራሉ።
በባህርዳር የብአዴን ባለስልጣናት ከፍተኛ ስብሰባ እያደረጉ ባለበት ወቅት በሁለቱ የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የስራ ማቆም አድማው መደረጉ፣ ለድርጀቱ መሪዎች ትልቅ ውድቀት መሆኑን አስተባባሪዎች ይገልጻሉ።
የመጨረሻው የነጻነት ደወል እስኪደወል ትግሉ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመ እንደሚዘልቅም አስተባባሪዎቹ ሙሉ እምነት አላቸው። በሌላ በኩል በጎንደር ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ በከተማው ህዝብ ዘንድ ወደር የለሽ ጀግና ተብላ የምትታወቀዋ ወጣት ንግስት ይርጋ በደህንነት ሃይሎች ታፍናለች። ወጣት ንግስት ታች አርማጭሆ ሳንጃ ከተማ ወደሚገኘው ቤቷ ስታመራ መያዙዋንና ወደ ማእከላዊ እስር ቤት መወሰዷ ታውቋል።
በ20ዎቹ የእድሜ ክልል የምትገኘው ወጣት ንግስት ፣ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱን ለመያዝ ሙከራ በተደረገበት ወቅት፣ ህዝባዊ ትግሉን በግንባር የመራችና ያስተባበረች መሆኗን በቅርብ የሚያውቋት ሰዎች ይናገራሉ።
በጀግንነቷ የብዙዎችን ልብ የማረከችው የወጣት ንግስት መያዝ የከተማውን ህዝብ በእጅጉ አበሳጭቷል። አገዛዙ ወጣቱዋን በአስቸኳይ እንዲለቃትም ጠይቀዋል።
ሌላው ታጋይ የአርማጭሆ ጀግና በመባል የሚወደሱት ሻለቃ ይላቅ አቸነፍ በህወሃት አገዛዝ በግፍ ተረሽነዋል። የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት ሻለቃ ይላቅ፣ ከአመት በፊት የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነትን ደግፈሃል በሚል ከትክል ድንጋይ ከተማ ተይዘው ወደ ቂልንጦ ተወስደው ነበር። ሻለቃ ይላቅ በእስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ ከደረሰባቸው በሁዋላ በጥይት ተደብድባው መገደላቸውንና በእሳት እንደተቃጠሉ ተደርጎ አስከሬናቸው መስከረም 5 ለቤተሰባቸው ተሰጥቷል።
ከወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጋር በተያያዘ ከሰሜን ጎንደር ተይዘው የመጡ የአካባቢው ተወላጆች ቂሊንጦ ውስጥ በጥይት ሆን ተብለው እንዲረሸኑ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ። የሟቾቹን ማንነት ለመለየት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በቅርቡ ከሰሜን ጎንደር የተለያዩ ከተሞች ተይዘው ወደ ቂልንጦ የገቡ ዜጎች ሁሉም መረሸናቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በቂልንጦ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግፍ ለማወቅ ኢሳት ምርመራውን የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህ አጋጣሚ የቪዲዮ የድምጽና ሌሎችም ማስረጃዎች ያሉዋቸው በኢሳት ስልኮች ወይም በኢሜል አድራሻችን መልእክቶችን እንድትልኩ እንጠይቃለን። በሌላ በኩል ደግሞ በብአዴን ስብሰባ ከፍተኛውና የታች አመራሩ መስማማት አለመቻሉ ታውቋል።
በባህር ዳር ከተማ የክልሉ ምክር ቤት ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ከወረዳ ጀምሮ እስከ ብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ያሉ አመራሮች ስብሰባ ቅዳሜ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጀመርም በአመራሮች መካከል በተነሳው አለመግባባት እሁድን አልፎ ሰኞንም በመጨመር ለሁለተኛ ቀን ተራዝሞ ቀጥሏል፡፡
ስብሰባውን የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን፣ ህላዊ ዮሴፍ፣ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሰ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው። በስብሰባው ላይ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል “በቅድሚያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ያወጁት ጦርነት እና የግድያ ትዕዛዝ በይፋ ሊያነሱ ይገባል፤ ለዚህም የጦር ኃይሎች አዛዥ ሆነው በሀገሪቱ ዜጎች ላይ እንዴት የግድያ ትዕዛዝ
ያዝዛሉ?በዚህ ትዕዛዝ ማግስት በአምባ ጊዮርጊስ በርካታ ወጣቶች በጦር ኃይሉ የተገደሉበትን ሁኔታ በማንሳት ይህን ምላሽ ከእናንተ ሳይሆን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንጠብቃለን” በማለት የታች አመራሮች ከፍተኛ አመራሮችን አፋጠዋል።
ከወረዳ ጀምሮ ያሉ አመራሮች በድፍረት ከፍተኛ አመራሩ ለአማራ ህዝብ ምንም እንዳልሰራ ተናግረዋል። አብዛኞች የዞንና የወረዳ አመራሮች ከመንግስት ስራ ላይ በመሆናችን ከዚህ በኋላ ወደ መደበኛ ስራችን
እንጅ ወደ ፖለቲካ አመራርነት መመለስ አንፈልግም ወንበራችሁን ተረከቡ ያሉ ሲሆን፣ የበታች አመራሩ በከፍተኛ የብአዴን አመራሮች ማፈሩንና ምንም መፈየድ የማይችሉ መሆኑን ያወቁበት ጊዜ ላይ መድረሳቸውን በግልጽ ተናግረዋል።
በእያንዳንዱ የተቃውሞ ንግግር ከፍተኛ ጭብጨባ የተሰማበት፣ በስብሰባው ማንኛውም አመራር ምንም አይነት ሞባይል ይዞ እንዳይገባ የታገደበት፣ አመራሮች ለሻሂ ሲዎጡ ከማንኛውም የመስተንግዶ ሰራተኛ ጋርና ከክልል ምክር ቤት ሰራተኞች ጋር እንዳያወሩ የታገደበት፣ የትኛውም የመንግስት ጋዜጠኛ እንዳይገባና ዘገባውን እንዳይከታተል የተደረገበት እንዲሁም እያንዳንዱ ተሰብሳቢ በቀን 3 ጊዜ እየተፈተሸ የሚገባበት ስብሰባ” የብአዴን ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ያመላከተ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።
ለህዝባዊ አመጹ መነሻ የሆነውን የወልቃይት ጉዳይ ‹‹ከፌደራል መንግስት በተሰጠን አቅጣጫ መሰረት…..›› በማለት አይነኬ ጉዳይ እንደሆነ የበላይ አመራሮች የበታች አመራሮችን ለማሳመን ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፡፡
‹‹የወልቃይትን ጉዳይ ካልፈታን የህዝቡን እንቅስቃሴ እንደምን ልንገታው እንችላለን? ›› ለሚለው ጥያቄ ‹‹ጉዳዩን በፌደራል መንግስት የበላይ አመራርና በመከላከያ ሰራዊቱ ጥንካሬ እንወጣዋልን ››
የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተሳታፊዎችን በመጥቀስ ዘጋቢያችን ገልጿል።