በኒውዮርክ ሮሽስተር እና ካናዳ ኤድመንተን ለኢሳት የገቢ ማሰባሰብያ ዝግጅት ከ100ሺ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

ኢሳት (መስከረም 9 ፥ 2009)

ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ኒውዮርክ ግዛት ሮችስተር እና በካናዳ ኤድመንተን ከተማ የሆነ ኢትዮጵያውያን በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜና እሁድ ኢሳትን ለመደገፍ ባካሄዱት ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ከ100ሺ ዶላር (ከሁለት ሚሊዮን ብር) በላይ ለገሱ።

የኢሳትን ስድስተኛ አመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ በሁለቱ ከተሞች በተካሄደው በዚሁ ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በርካታ ኢትዮጵያውያን በመታደም ኢሳትን ለመደገፍ ፈቃደኝነታቸውን እንዳሳዩ የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች ለዜና ክፍላችን ገልጸዋል።

በካናዳ ኤድመንተን ከተማ በተከናወነው ዝግጅት ከ500 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመገኘት ለኢሳት ያላቸውን ድጋፍ በደማቅ ሁኔታ እንዳሳዩ አስተባባሪዎች ገልጸዋል።

በዚሁ ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት የአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ሌሎችም የነጻነት ታጋዮች ምስል ለጨረታ የቀረበ ሲሆን፣ በእለቱም ከዚሁ የጨረታ ሽያጭና ከተደረጉ ድጋፎች ወደ 65ሺ ዶላር አካባቢ መሰብሰቡ ታውቋል።

የኢሳትን ስድስተኛ አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ የተካሄደው ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት የተሳካ እንደነበር አስተባባሪዎቹ የገልጹ ሲሆን፣ ኢሳትን በመወከል አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ተገኝተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ እሁድ በዚህ በአሜሪካ ኒው ዮርክ ግዛት ሮችስተር ከተማ በተካሄደ ዝግጅት በዕለቱ የታደሙ ኢትዮጵያውያን ከ35ሺ ዶላር በላይ ማሰባሰባቸውን የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ለዜና ክፍላችን አስረድተዋል።

በሮችስተር ከተማ በተካሄደው በዚህ የልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ኢሳትን በመወከል ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፣ እንዲሁም ኮሜዲያን ክበበው ገዳ ተገኝተዋል።

በኢሳት የአመቱ ምርጥ ሰው ሆነው የተመረጡት የኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ፣ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ የአቶ በቀለ ገርባና የአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ምስል በዚሁ ዝግጅት ለጨረታ ቀርቦ የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ ከ35ሺ ዶላር በላይ ገንዘብ መገኘቱ ታውቋል።

በሁለቱ ከተሞች በተከናወኑት ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በአጠቃላይ ከ100ሺ ዶላር (ከሁለት ሚሊዮን ብር) በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን የኢሳት አለም አቀፍ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታውቋል።

የኢሳትን ስድስተኛ አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶችና ሃገራት ሲካሄድ የቆየው ዝግጅት ቀጣይ እንደሚሆን ኮሚቴው አክሎ ገልጿል።