በምዕራብ ጎጃም ቡሬ ከተማ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ተካሄደ

ኢሳት (ነሃሴ 18 ፥ 2008)

ባለፉት ሳምንታት በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ዛሬ አርብ በምዕራብ ጎጃምና በሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ መዋሉ ተነገረ።

በምዕራብ ጎጃም ቡሬ ከተማ ዓርብ እለት በተካሄደው በዚሁ ተቃውሞ፣ ከህወሃት/ብዓዴን ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ የንግድ ድርጅቶች ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው ለማወቅ ተችሏል። የብዓዴን የንግድ ድርጅቶች ንብረት የሆኑ እንደ “አማራ ብድርና ቁጠባ” አይነት ድርጅቶች ላይ ጥቃት መድረሱን የአይን እማኞች ከስፍራው ለኢሳት ገልጸዋል።

በራስ ተነሳሽነት ለሰላማዊ ሰልፍ በነቂስ የወጣው የቡሬ ከተማና አጎራባች መንደሮች ህዝብ፣ የብዓዴን የድርጅት አርማም እንዳቃጠለ፣ “ወያኔ ሌባ” በማለት ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደዋሉ ለማወቅ ተችሏል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አደባባይ የወጣውን የከተማዋን ነዋሪ ለመበተን የተኩስ ዕርምጃን ጨምሮ የተለያዩ የሃይል እርምጃዎችን በመጠቀማቸው አንድ ሰው መገደሉን፣ እንዲሁም ሌላ አንድ ሰው መቁሰሉ ታውቋል።

ህዝባዊ ተቃውሞው በሌሎች አነስተኛ አጎራባች ከተሞችም ተጠናክሮ መቀጠሉ ከስፍራው ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያስረዳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በፍኖተ ሰላም ከተማ ሃሙስ እለት በአንድ ላይ የግድያ እርምጃ ወስዷል ተብሎ የተጠረጠረ የፖሊስ አባል ተላልፎ እንዲሰጣቸው የፍኖተ ሰላም ከተማ ወጣቶች እየጠየቁ መሆኑ ተነግሯል። ሰልፈኞቹ “ወያኔ ሌባ” እያሉ በህብረት ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ከፍኖተ ሰላም ወደ ባህርዳር በሚወስደው ዋና መንገድ በ10 ኪሎሜትር እርቀት ላይ በምትገኘው ማንኩሳ ከተማ ትናንት በተቀሰቀሰ ህዝባዊ ተቃውሞ ሃሙስ ዕለት አንድ ሰው መሞቱን እና ሁለት ሰዎች መቁሰላቸው እማኞች ለኢሳት ከስፍራው ገልጸዋል። በራስ ተነሳሽነት የተደራጁ ወጣቶች የተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት በእሳት ማጋየታቸውን ኢሳት ከደረሰው የምስል ማስረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በተያዘው ሳምንት ወደ አዳዲስ አካባቢዎች በመዛመት ላይ መሆኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል። ህዝባዊ ተቃውሞ በተለይም በሰሜን ጎንድር አድማሱን በማስፋት በትንንሽ ከተሞች ጭምር በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ ታውቋል።