አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ አገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላደረጉለት ድጋፍና ማበረታቻ ምስጋና አቀረበ

ኢሳት (ነሃሴ 18 ፥ 2008)

በታላቁ የሪዮ ዴ ጄኔሮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነውና በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስት ሃይሎች እየተፈጸመ ያለውን ግድያ፣ አፈናና፣ እስራትን በመቃወም በአለም መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሽፋን ያገኘው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላደረጉለት ድጋፍና ማበረታቻ ምስጋና አቀረበ።

አትሌት ፈይሳ ለጀርመን ዶቼ ዌሌ የዜና አገልግሎት ድርጅት በሰጠው ቃለምልልስ፣ የማራቶን ወድድሩን ለመጨረስ ጥቂት ሜትሮች ሲቀረው ባሳየው ተቃውሞ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ድጋፍ ስለቸሩት ክብር እንደተሰማው ገልጿል።

በኢትዮጵያና በሌሎች ውጭ አገራት የሚኖሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በስልክ፣ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንና በአካል ጭምር የማበረታቻ ድጋፍ እንዳደረጉለት አትሌቱ ለዜና ወኪሉ በሰጠው ቃለመጠይቅ አብራርቷል። “ኢትዮጵያውያን ባደረጉልኝ ድጋፍና ማበረታቻ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፣ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ” ማለቱን ዶቼ ዌሌ ዘግቧል።

የወቅቱን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳት በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጥ የተጠየቀው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፣ “የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይገኛል፣ ሆኖም ህዝቡ የንቅናቄውን አድማስ በማስፋት አላማው እስኪሳካ ድረስ ድምጽ ማሰማቱን መቀጠል አለበት” ሲልም ምክር ለግሷል።

አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በአለም አቀፍ መድረክ የስፖርት ውድድር የሚያደርጉ አትሌቶች አጋጣሚውን ተጠቅመው የኢትዮጵያ ህዝብ በመንግስት የሚደርስበትን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ለአለም ህብረተሰብ እንዲያጋልጡ ጥያቄ ማቅረቡን ዶቼ ቬሌ የእንግሊዝኛው አገልግሎት በድረገጹ ላይ አስፍሯል።

በአለም አቀፍ መገኛኛ ብዙሃን ዘንድ አሁንም ድረስ መነጋገሪያ ሆኖ የሚገኘው አትሌት ፈይሳ በሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ድሉ ወቅት እጆቹን ከጭንቅላቱ በላይ በማጣመር በሃገሪቱ እየተፈጸመ ያለውን ግድያ ማውገዙ ይታወሳል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ያሳየውን የጀግንነት ተግባር በመደገፍ በጥቂት ቀናት ከ147 ሺ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰቡን ከአዘጋጆቹ ለመረዳት ተችሏል።

አትሌቱ በውድድሩ ወቅት ያስተላለፈው ፖለቲካዊ መልዕክት ከኦሎምፒክ ህግ አንጻር ተጻራሪ ሊሆን ይችላል በማለት የአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጉዳዩን እንደሚመለከተው ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ኮሚቴው  አትሌትው ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ማጠናቀቂያ ወቅት ላሳየው ተቃውሞ የሚወስደው እርምጃ እንደማይኖር ትናንት ሃሙስ ማረጋገጡን መዘገባችን ይታወሳል።