ነሃሴ ፲ ( አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ተመሳሳይ ተቃውሞች በሌሎች ከተሞችም ይደረጋሉ
በጎንደር በአደባባይ ሲደረግ የነበረው ተቃውሞ ወደ ስራ ማቆም እና ከቤት ያለመውጣት አድማ ከተቀየረ በሁዋላ ፣ ሁሉንም የከተማዋ ነዋሪዎች በአንድነት ያሳተፈ የስራ ማቆም እና ከቤት ያለመውጣት አድማ ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተካሄደ ነው። ካለፉት ሶስት ቀናት ጀምሮ የንግድ ድርጅቶች አልተከፈቱም፣ ታክሲዎች አውቶቡሶች እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ስራ አቁመዋል። ወደ ቤተክርስቲያን ወይም ወደ መስኪድ ለመሄድ ካልሆነ በስተቀር ጎዳና ላይ ዝር የሚል ሰው የለም። የመንግስት ሰራተኞችም ሆኑ በግል ስራ የሚተዳደሩት ሁሉ የአድማውን ጥሪ ተቀብለው በአንድነት እየተገበሩት ሲሆን አቅም ያላቸው ለሌለው ምግብ እያቀበሉ ነው። በአንድ ምሽት የመልዕክት ቅብብል የተጀመረው አድማ አስደማሚ ሆኖ መቀጠሉን የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
መልእከቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደተላለፈ ሁሉም ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረጉን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ሁሉም ነገር ቆሟል ሲዞሩ፣ የሚታዩት ወታደሮች ብቻ ናቸው ይላሉ። ወታደሮች ሱቅ ክፈቱ እያሉ ለማስፈራራት ቢሞክሩም፣ ማንም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም
“ከተማው የተወረረ መስሎአል” የምትለው ሌላዋ ነዋሪ፣ እየተካሄደ ያለው ነገር እንዳስደሰታት ትገልጻለች። በተለያዩ ቀበሌዎች የሚገኙ ወጣቶች በግል ተሰባስበው ለተቸገሩት እንጀራ እና ውሃ በማቅረብ ላይ እያሉ ፖሊሶች ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ በማለት አንዳንድ ወጣቶችን ለመደብደብ መሞከራቸውንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ትናንት ሰኞ ደግሞ በወገራ ወረዳ አምባ ጊዮርጊስ ከተማ ወጣቶች መታሰራቸውን ተከትሎ፣ የከተማው ህዝብ ተቃውሞውን ያሰማ ሲሆን፣ ወታደሮች በህዝቡ ላይ በመተኮስ ለመበተን ሞክረዋል። ጥይት ያልበገራቸው ወጣቶች ወደ እስር ቤት በመሄድ ጓደኞቻቸውን ማስፈታታቸው ታውቋል። ሶስት የፖሊስ አባላትም ቆስለዋል።
በእብናት ከተማ ደግሞ ትናንት ወጣቶች ከፖሊሶች ጋር ተደባድበዋል። ዛሬ በርካታ ወጣቶች ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ የታሰሩት እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ወጣቶች አንፈተሽም አንገዛም ማለታቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ውጥረቱ አሁንም እንዳለ ነው ይላሉ።
በእብናት ከሳምንት በፊት 15 የጦር መሳሪያዎች ከግምጃ ቤት መዘረፋቸው ይታወቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ 4 ፖሊሶች ታስረው የነበረ ሲሆን፣ ሶስቱ ተለቀው አንዱ ብቻ አሁንም በእስር ላይ ይገኛል። በደብረማርቆስ ከተማም እንዲሁ ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶቻቸውን በመዝጋት የስራ ማቆም አድማ መጀመራቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ገዢው ፓርቲ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄዱ ተቃውሞችን በሃይል ለማፈን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ቀጥሎበታል። ደሴ አሁንም በወታደሮች እንደተከበበች ናት። በርካታ ወጣቶች እየተያዙ ወደ እስር ቤት እየተጋዙ ነው።
ነሐሴ 1/2008 ዓም በመቶ ሽዎች በሚቆጠሩ የባህርዳርና አካባቢው ሰዎች በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ተካፍላችኋል በሚል ያለጥፋታቸው ታስረው ከነበሩት በሺዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል 180 ያህሉ በህብረተሰቡ ግፊት ተለቀዋል፡፡ እስረኞቹ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጽንሰ ኃሳብና በፌደራሊዝም አወቃቀር ዙሪያ ሃገሪቱ እየተከተለች ያለውን መስመር በትምህርት ሲሰጣቸው እንደቆዩ የተናገሩ ሲሆን፣ በወንድአጣ አካባቢ በሚገኘው አዲስ እስር ቤት ያለምንም ምግብ ሲሰቃዩ ሰንብተዋል።
ከእስር የተለቀቁት ወጣቶች ትግላቸውን እንደማያቆሙ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል።